ቀጥታ፡

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንዲለሙ መደረጉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት አሳድጓል

ደሴ ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንዲለሙ መደረጉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን አሳድጎታል ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን በሐይቅ ከተማ የጀልባ አከራይና አስጎብኚ  ወጣቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዞኑ ከቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ጋር በተያያዘ በዘርፉ ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡ ወጣቶች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሐይቅ ከተማ ነዋሪ ወጣት አደፋ አህመድ  እንደገለጸው፤  በጀልባ ማከራየት ስራ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ ህይወቱን እየመራ ይገኛል።


 

ከሰርግና ከሌሎች ዝግጅቶች ጋር ተያይዞ  ለጎብኝዎች በሀይቅ ላይ የጀልባ ትራንስፖርት እየሰጠ መሆኑን አመልክቷል ።

መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት በአካባቢያችን ያሉ ፀጋዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እያደረገ ያለው ጥረት በዘርፉ የበለጠ ሰርተን ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ተስፋ አሳድሮብናል  ብሏል።

በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችም መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ  መሆኑን ጠቁሞ ይህም የጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምርና የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝም በመሆኑ ተጠቃሚነታችንን ያሳድገዋል ብሏል።

ሌላው ወጣት አደም መሀመድ፣ በጀልባ ቱሪስቶችን በማጓጓዝ በሚያገኘው ገቢ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ይናገራል።


 

አሁን ላይ በአካባቢው  የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እየለሙ መሆኑን ጠቅሶ፤ ለዚህ የሚመጥኑ ፈጣን ጀልባዎችን በማቅረብ የገቢ አቅሙን ለማሳደግ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የጀልባ ባለንብረቶች በማህበር ተደራጅተን ቱሪስቶችን በማጓጓዝ ተጠቃሚ እየሆንን ነው ያለው ደግሞ የማህበሩ ሰብሳቢ ሁሴን ሰይድ ነው።


 

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አካባቢያችን እየለማ በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች ወደ አካባቢያችን ይመጣሉ፣ እኛም የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን  ብሏል።

ለዚህም አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ቱሪስቶችን ከማስጎብኘት ባለፈ የአካባቢያችን የአብሮነት፣ የፍቅርና የመቻቻል ባህል በማስተዋወቅ የድርሻችንን እንወጣለን ሲልም አመልክቷል።


 

ወጣቶቹ በከተማው እየተሰራ ያለውን የኮሪደር ልማት ጨምሮ ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ልማቶችም እየተፋጠኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አስያ ኢሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በዞኑ ከ60 በላይ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ተለይተዋል።


 

የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት ባለፈ አንዱን ከሌላው ጋር በማስተሳሰር ጭምር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እና ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

በዞኑ አራት ሐይቆች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ በሐይቆች መዳረሻ መሰረተ ልማት የማሟላትና ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም