የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ምህዳርን እየፈጠሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ምህዳርን እየፈጠሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ምህዳር እየፈጠሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ማሻሻያዎችና የሪፎርም ስራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ መከናወናቸው የሚደነቅ ነው።
በዘርፉ ገበያ ተኮር ስርዓት ለማስፋፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ተመልክተናል፤ ይህም አስፈላጊ መሆኑን የጀርመን ልምድ ያመለክታል ብለዋል።
ይህ ስርዓት ለህዝቦች ተጠቃሚነትና ዘላቂ ብልጽግና ውጤታማ መሆኑን በጀርመን የተገኙ ውጤቶች እንደሚያሳዩ ገልጸው፤ የጀርመን ባለሀብቶችንም ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ምህዳር እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ምክትል አምባሳደሩ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አክሲዮን ገበያ ልውውጥ (stock market excahnge) ክፍት መደረጉ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት ለመሳብ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች፣ በሎጂስቲክስና በሌሎች ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ ጠንካራ ስራዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ከአውሮፓ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነትን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ይህም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ ጥራትና አገልግሎት ለማሻሻል በአጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማነቃቃት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በበርካታ ዘርፎች እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም መኖሩን ምክትል አምባሳደሩ አንስተዋል።
ለአብነትም በአረንጓዴ የሀይል ምንጭ በታዳሽ ሀይል ዘርፍ እምቅ አቅም መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህ ለዓለም ገበያ ብራንድ መሆን ይችላል ብለዋል።
በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ፣በሎጂስቲክስ፣ ጉምሩክ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች እምቅ አቅሞች መኖራቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ምቹና ተወዳዳሪትን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያና የጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ከሆኑት የጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
በግብርና፤ የግል ሴክተር፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ፣ በትምህርት ምርምርና ጥናት መልካም አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎች ለብዙ አመታት የዘለቀና ጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብር መኖሩን አንስተዋል።
ኢትዮጵያና ጀርመን የሶስት ዓመት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ከ2025–2027) በቅርቡ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ማዕቀፉ የሀገሪቱን ሪፎረም፣ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እና ዘላቂ ልማትና ትብብር ላይ ያተኮረ ነው።