ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው

‎ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት፤ የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

‎በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በ9 ሺህ 206 ተፋሰሶች ላይ በ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ቀጥሏል ብለዋል።

የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ‎እስከ መጪው መጋቢት ወር የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ የልማት ስራ ላይ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ መሆኑን አንስተው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብርና ተሳትፎም መጠናከር አለበት ብለዋል።

‎በበጋው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የማሳና የጋራ ላይ እርከን፣ የውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦዮች እንዲሁም ከ6 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

‎በክልሉ የልማት ስራው ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ‎የደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አራጋው ወንዴ እና በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ዙሪያ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ ይመር፤ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ መሰረታዊ ጉዳይ አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።

‎በዚህ የልማት ስራ የእርሻ መሬትና የአፈር ለምነት እንዲሻሻልና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ በተፋሰሶቹ የእንስሳት መኖ ማግኘት እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል። 

‎በክልሉ ባለፈው ዓመት በ8 ሺህ 400 ተፋሰሶች ላይ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ መከናወኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም