በክልሉ ለዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ቦንጋ ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዘንድሮ ከ272 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የመሬትና የውሃ ሀብትን መጠበቅ፣ ማልማትና በላቀ ደረጃ አቀናጅቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በየዓመቱ የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር ለምነትን ለመመለስና የውሃ ሀብትን ለማበልፀግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ምርትና ምርታማነት መጨመሩን ያነሱት አቶ ውብሸት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የለሙ አካባቢዎች ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም ገልጸዋል።
ዘንድሮም ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ ከጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 30 ቀናት በሚከናወነው የአፈርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ1 ሚሊዮን 305 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡
የዘንድሮ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በ1ሺህ 210 ተፋሰሶች በሚገኝ 272 ሺህ 250 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚከናወንም አቶ ውብሸት አስታውቀዋል።
ለሥራው ውጤታማነት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት፣ ለልማቱ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ማሟላት እንዲሁም የልማቱ ተሳታፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን መለየትና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።