በደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው
ደሴ ፤ ታሕሳስ 8/2018(ኢዜአ)፡ -በደሴ ከተማ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ቀልጣፋ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ ተገልጋዮች ተናገሩ።
በከተማው ተቋማት የሕዝብን መስተንግዶ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ያለበት ለማድረግ በቅርቡ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተገልጋዮች ይናገራሉ።
ከተገልጋዮች መካከል ወይዘሮ ፈንታዬ ንጉስ፤ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ መጀመር ሁሉንም አገልግሎቶች አንድ ቦታ ላይ ማግኘት አስችሎናል ብለዋል።
ቀደም ሲል ጉዳያቸውን ለመፈፀም ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ ከመመላለስ ባለፈ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸው እንደነበረ አስታውሰው፤ አሁን ላይ በመሶብ አንድ ማዕከል ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
ካገኙት አገልግሎት ውስጥ ፋይዳ መታወቂያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ትህትና በተሞላበት አቀባበል ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ተገልጋይ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ ሁሉንም አገልግሎቶች በተደራጀ አግባብ በአንድ ቦታ ለማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
በተለይ አሰራሩ በቴክኖሎጂ ጭምር የተደገፈ መሆኑ እንግልትንና ብልሹ አሰራርን ከማስቀረቱ ባለፈ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም የሚያደርግ ሆኖ እንዳገኙት አንስተዋል።
የተሽከርካሪ እና የመንገድ ፈንድ አገልግሎት ፈልገው መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ አህመድ፤ ቀደም ሲል ባለሙያ በሰዓቱ ካለመግባቱ ባለፈ ብዙ ወረፋ እየጠበቁ ለእንግልትም ይዳረጉ እንደነበረ አስታውሰዋል።
አሁን ከበር ጀምሮ ጉዳያቸውን ጠይቀው አገልግሎት መስጫው ድረስ የሚወስዱ ባለሙያዎች መመደባቸው ይገጥም የነበረውን መደነጋገር ያስቀረና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ወደ ሌሎች ከተሞች መስፋት ያለበት ነው ብለዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል ያሉት ደግሞ በደሴ ከተማ አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የስም ንብረትና ዝውውር ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ውለታው ናቸው።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ባለሙያ ወይዘሪት ዓለም እሸቱ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የመንገድ ፈንድ፣ ፋይዳ መታወቂያና ሌሎችንም ፈጣን መልዕክት አገልግሎቶች እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን በዛብህ እንዳሉት፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነት ያለበት አስራር በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመቻችቷል።
በዚህም መሬት ነክ፣ ገቢዎች፣ ንግድ፣ የቴሌኮም፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የባንክ፣ የኢሜግሬሽንና ፋይዳ መታወቂያን ጨምሮ 79 አገልግሎቶች በማዕከሉ እየተሰጡ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከደሴ በተጨማሪ በባሕርዳር ከተማ የተጀመረ ሲሆን፤ በሌሎች ከተሞችም የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።