ቀጥታ፡

በዞኑ የተሻሻለ የግብርና አሰራር በመጠቀም ከለማው መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

አዶላ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የተሻሻለ የግብርና አሰራር በመጠቀም ከለማው መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት  እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የኦሮሚያ ክልል፣ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ሞዴል አርሶ አደሮች በዞኑ አናሶራ ወረዳ የልምድ ልውውጥና የሰብል ልማት ምልከታ አድርገዋል፡፡


 

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ደስታ ገብረየስ  እንደገለጹት፤ በዞኑ በመኸር የአዝመራ ወቅት ከለማ ሰብል ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

የመኸር እርሻው ኩታ ገጠምና የመስመር አስተራረስ ዘዴን ጨምሮ ሁሉንም የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም መከናወኑንም አመልክተዋል።


 

ከዚህም ባለፈ የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አጠቃቀም እየተሻሻለ በመምጣቱ ዘንድሮ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በዞኑ አጠቃላይ ከ480 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ጤፍና በቆሎ ሰብሎች መልማቱን ጠቅሰው ይህም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።


 

ከለማው መሬት ውስጥ ከ347 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ጠቅሰው በዞኑ 12 ወረዳዎች በተመደቡ 267 የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ለአርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ ድጋፍና እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በምልከታው ላይ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የስርአተ ምግብ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሸምሲያ ወልይ፣ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የቤተሰብ ብልጽግና ማምጣት የክልሉ መንግስት ትኩረት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡


 

በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአፈርና ውሀ ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ለውጦችና ስኬቶች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በጉጂ ዞን በተሻሻለና በዘመነ የግብርና አሰራር የለማው ሰብል አጠቃላይ ለክልሉ ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

በምልከታው ላይ የተገኙት ሞዴል አርሶ አደር ደበሶ ሶራ፣ ባለፉት ዓመታት ያካሄዱት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ለምርት መጨመር እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


 

በልማት ጣቢያ ሠራተኞችና በተሻሻለ አሰራር በመታገዝ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ሰብል የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ የልምድ ልውውጡም ተጨማሪ አቅም ያገኙበት መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላው ሞዴል አርሶ አደር ገዳ ዴከማ፤ የለውጡ መንግስት ግብርናን በማሻሻል አርሶ አደሩን ከሰብል ልማት የተሻለ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለመኸር አዝመራቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የስንዴ፣ ገብስና ባቄላ ምርጥ ዘር በግብርና ቢሮ በኩል መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ 


 

በጉጂ ዞን ደጋ ወይናደጋና ቆላማ አየር ጸባይ ያለ ሲሆን ከነሀሴ እስከ መስከረም አጋማሽ የዝናብና የዘር፤ ከታህሳስ እስከ የካቲት አጋማሽ ደግሞ የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ነው፡፡

በልምድ ልውውጡና በሰብል ልማት ጉብኝቱ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም የወረዳ የዞንና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም