ቀጥታ፡

ሕንድ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 8/2018(ኢዜአ)፡- ሕንድ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡


 

በንግግራቸውም፤ የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቁመው፤ ታሪክና ባህል የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ሕንድ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ሴኩሪቲ፣ በዐቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላትም አመላክተዋል።

በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍም የሕንድና ኢትዮጵያ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም መሠረት በይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።


 

ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ላለመገዛት በልበ ሙሉነትና በአንድነት ያደረጉት ተጋድሎና ያገኙትን ድል አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁንም በቀጣናው ያላትን የሰላምና መረጋጋት ሚና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

በዓለም መድረኮችም ሕንድና ኢትዮጵያ ያላቸውን ድምፅ በማስተባበር ለታዳጊ ሀገራት መብት መከበር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም