ቀጥታ፡

የዲላ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማት እንዲስፋፋ ድጋፍ እያደረጉ ነው

ዲላ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በዲላ ከተማ እየተከናወነ ላለው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ መስፋፋት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ባለሙያዎች ቡድን በከተማዋ የተሰራውን የኮሪደር ልማት ጎብኝቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በዲላ ከተማ የተከናወነው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረጉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።  

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መክሊት ሆርዶፋ፤  የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን የተደበቀ ውበት በማውጣት ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም የመንገድ ጥበት ከመኖሩ ባለፈ ምቹ የእግረኛ መንገድ ባለመኖሩ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ፍሰቱን ጨምሮ በከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ልማቶች ለቀጣይ ትውልድ ጭምር የሚሻገሩ ናቸው ያሉት ወይዘሮ መክሊት ለልማቱ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ በማጠናከር ለከተማዋ ዕድገት መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ነብዩ ጎበና በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ዲላ አዲስ ገጽታ እንድትላበስ በማድረግና ለእንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል። 


 

ልማቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ መፍጠሩንና የንግድ እንቅስቃሴን ማነቃቃቱን ጠቁመዋል።

እሳቸውን ጨምሮ የከተማዋ ህብረተሰብ ልማቱ እንዲፋጠን በተለያየ መንገድ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፣ በከተማው አሁን ለመጣው ለውጥ የነዋሪዎች ድርሻ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ናቸው።

በዚህም በከተማዋ 21 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለመስራት ታቅዶ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል። 


 

የኮሪደር ልማት ሥራው ለከተማዋ መግቢያ በር፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛና ብስክሌት መንገድን ጨምሮ መዝናኛ ስፍራዎችን አካቶ መሰራቱንም አመላክተዋል። 

በልማቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው በዚህም ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረ 654 ሚሊዮን ብር ለማዳን ተችሏል ብለዋል።

በከተማዋ በህዝብ ተሳትፎ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባው፣ በሁለተኛው ምዕራፍ በህብረተሰቡ ተሳትፎ 11 ኪሎ ሜትር የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለማከናወን ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ተናግረዋል።


 

ልማቱም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የከተማዋ ነዋሪዎች ለልማቱ መሳለጥ እያደረጉት ባለው ቀና ትብብር ያመሰገኑት ከንቲባው፣ ነዋሪዎች ለከተማዋ እድገት መፋጠን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም