የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በማበልጸግ ለመላው ዓለም ምሳሌ እንድትሆን ያስችላል - የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በማበልጸግ ለመላው ዓለም ምሳሌ እንድትሆን ያስችላል - የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር እየተተገበረ የሚገኘው የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በማበልጸግ ለመላው ዓለም ምሳሌ እንድትሆን ያስችላል ሲሉ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ፡፡
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የስራ ጉብኝት በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ በመገኘታቸው እድለኛ መሆናቸውንና በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመው የዓለም የስልጣኔ ምንጭ ከሆነችው ኢትዮጵያ የክብር ኒሻን በማግኘቴ ኩራት ተሰምቶኛል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የክብር ኒሻኑ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ያደረጉ ህንዳውያን እና ኢትዮጵያውያን ጭምር ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው የጂ 20 ጉባዔ ጎን ለጎን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በቀረበላቸው ግብዣ መደሰታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ያለኝ ፍቅር ግብዣውን በመቀበል በፍጥነት እንድመጣ አድርጎኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ፤ ክብር እና ነጻነት ለሁላችንም መነሳሳትን የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን በማበልጸግ ለመላው ዓለም ምሳሌ እንድትሆን ያስችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በተለይም በአካባቢ ጥበቃ፤ በአካታች ልማት፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ላለው ቁርጠኝነት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ትምህርት በህንድ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና ህንድ በቀጣይ በራዕይና መተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን የማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር አዳዲስ እድሎችን የሚፈጥሩ ግንኙነቶች ለመመስረት እንደምትሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡