ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይደረጋሉ። 

ባህር ዳር ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል። ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር 16 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

በሊጉ ካከናወናቸው 12 ጨዋታዎች መካከል አንዱን ብቻ ያሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ ዘጠኝ ሽንፈቶችን አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል። አምስት ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር 24 ግቦች ተቆጥረውበታል።

አዲስ አበባ ከተማ በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።

ጨዋታው ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ፣ አዲስ አበባ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርጉት ነው።

በሌላኛው መርሃ ግብር ሲዳማ ቡና ከይርጋ ጨፌ ቡና ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በአራቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 12 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ጎሎችን አስተናግዷል። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሲዳማ ቡና በ15 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ይርጋ ጨፌ ቡና በሊጉ ካካሄዳቸው 12 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፎ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አዲስ አዳጊው ይርጋ ጨፌ ቡና በ10 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። 

የዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር ልደታ ክፍለ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 12 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በዘጠኙ ሽንፈት ሲያስተናግድ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በ12ቱ ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 23 ግቦች ተቆጥረውበታል። 

ቡድኑ በአምስት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማ በበኩሉ ከ12 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ሰባት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

አርባ ምንጭ ከተማ በስምንት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ33 ነጥብ ሊጉን ይመራል።

ዳግማዊት ሰለሞን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በ17 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እያመራች ነው። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በዘጠኝ እና የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ማህሌት ምትኩ በስድስት ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም