ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ህንድ ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሸጋገር መወሰናቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ህንድ ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር መወሰናቸው ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና ህንድ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ሀገራቱ ጥልቅ ወዳጅነት፣ ትብብር እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

የህንድ አቋም ከኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው የአፍሪካ እና ህንድ አጋርነት አፍሪካ ባለቤት የሆነችበት፣ አፍሪካ መር እና በአፍሪካ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ህንድ በሉዓላዊነት፣ ራስን መቻል እና የተግባር ትብብር ላይ የተመሰረተውን ዘመናዊ አጋርነት የበለጠ ማጠናከርን ያለመ ነው ብለዋል።

የሁለትዮሽ ትብብሩ በእኩልነት እና የደቡብ ደቡብ አጋርነት መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የህንድ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ብሄራዊ አቅም፣ ሁሉን አቀፍ ልማት እና ነጻነት ያከበረ አጋርነት ላይ የተመረኮዙ መሆናቸው ያላቸውን የጋራ መጣጣም እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጠንካራ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ገልጸው በ2017 ዓ.ም የ9 ነጥብ 2 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ እድገት (ጂዲፒ) መመዝገቡን ገልጸዋል።

በ2018 ዓ.ም 10 ነጥብ 3 የጂዲፒ እድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

ከኢኮኖሚ እድገቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ህንድ የኢንቨስመንት ፍሰቱ መሪ ምንጭ ናት ብለዋል።

ከ615 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለያዩ መስኮች ያለው ግንኙነት እያደገ መምጣቱ በመተማመን ለተመሰረተው ለሁለቱ ሀገራት ትብብር ጠንካራ መሰረት እንደሚጥል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ህንድ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ መወሰናቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸው ቆይታቸው ፍሬያማ አንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም