ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ዕድገት የሚያሳልጥ የመንገድና ትራንስፖርት ሥርዓት እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ የዕድገት ሰንሰለት የሚያሳልጥ የመንገድና ትራንስፖርት ሥርዓት እየተፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት የመንገድና ትራንስፖርት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዲሁም የባለድርሻ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያን ብዝሃ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያሳልጥ የመንገድና ትራንስፖርት መሰረተ ልማት እየተገነባ ነው ብለዋል።

በዚህም የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሳቢ ያደረገ የመንገድና ትራንስፖርት ዘርፉን የሚያሻሽል የረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

የመንገድና ትራንስፖርት ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ በሥራ ላይ ለማዋልም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ግብዓት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፤ ረቂቅ ፖሊሲው የኢትዮጵያን የመንገድና የትራንስፖርት ዕድገት ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎትን ደኅንነቱ የተረጋገጠና ምቹ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ቅልጥፍና እና የኢኮኖሚ አማራጭን የሚያረጋግጥ፤ አረንጓዴ አካባቢና የህብረተሰቡ ጤናን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ረቂቅ ፖሊሲውን የባለድርሻ አካላትን ግብዓት በማከል የተሟላ ቅርጽ በማስያዝ ስራ ላይ እንዲውል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም የመንገድና ትራንስፖርት አስተዳደርና ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በረቂቅ ፖሊሲ ሰነዱ ላይ የተመላከቱ የልማት ተግባራት ምክረ ሃሳቦች ላይ ምክክር ተደርጎባቸዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ላይ የመንገድ መሠረተ ልማትን በማስፋት ሁለንተናዊ የዕድገት ትስስርን የሚያሳልጥ ዘመናዊ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

የመንገድና ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ የግብዓት አቅርቦት ፍላጎትን በተሻለ አሰራር መምራት የሚያስችል የሰው ሃብትና ሎጂስቲክስ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ተመላክቷል፡፡


 

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል አባሶ፤ ረቂቅ ፖሊሲው ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ አጠቃላይ የመንገድ ደህንነትና የህብረተሰቡ ደህንነት እንዲጠበቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ፤ ረቂቅ ፖሊሲው ሲጸድቅ ሁለንተናዊ የመንገድ አስተዳደር ሥርዓትን ማስጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም