በአካባቢያችን ያለውን ሰላም ለማጽናት በቅንጅት እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢያችን ያለውን ሰላም ለማጽናት በቅንጅት እንሰራለን
ሰቆጣ ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-መንግስት ለአካባቢያቸው ሰላም መፅናት እያከናወነ ላለው ተግባር ውጤታማነት በቅንጅት መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአምደወርቅ ከተማና የደሃና ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ የአምደወርቅ ከተማና የደሃና ወረዳ ነዋሪዎች ''ሁሌም ለሰላም ዘብ እንቆማለን'' በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ግንባታ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ ነዋሪዎቹ መንግስት ለአካባቢያችን ሰላም መፅናት እያከናወነ ላለው ተግባር ውጤታማነት በቅንጅት መስራታችንን የበለጠ እናጠናክራለን ብለዋል።
አስተያየት ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በደሃና ወረዳ የጭላ ቀበሌ ነዋሪ አይምሮ ንጉሱ፤ መንግስት የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ለዚህም ከመንግስት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የአምደወርቅ ከተማ ነዋሪ ቄስ አዳነ ምረቴ በበኩላቸው፤ መንግስት ለአካባቢያቸው ሰላም መጠበቅ ህብረተሰቡን በማስተባበር በመስራቱ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።
የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች እያደረጉ ያሉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ ናቸው።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ ለሰላም መፅናት ከመንግስት ጋር በመሆን እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል፤ ህብረተሰቡ ራሱን ከከፋፋይ አጀንዳ በመጠበቅ ለአካባቢው ሰላም መስፈን ከመንግስት ጋር እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከነዋሪዎቹ ጋር በተደረገው የሰላም ውይይት ላይም የሃገር መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።