ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የደንበኞቹን ፍላጎትና እርካታ መሰረት ያደረጉ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦ የአየር መንገዱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የደንበኞቹን ፍላጎት መሰረት ያደረጉና የተገልጋዮችን እርካታ የሚጨምሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት በአገልግሎት ጥራትና ልህቀት ጭምር ተጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያስገነባውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ላውንጅ ሥራ አስጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያጠናክር ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው።

ለዚህም በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሰለጠነ እና የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና ሌሎች የልህቀት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይነት የሚደረግ የመሠረተ ልማት ግንባታ አየር መንገዱ የሚያደርገውን የከፍታ ጉዞ እውን ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

በዛሬው ዕለት ሥራ የጀመረው የፕሪሚየር ላውንጅ አየር መንገዱ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን ክብር በግልጽ የሚያሳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

አየር መንገዱ ዕድገቱን ከአገልግሎት ጥራት በማስተሳሰር ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማላቅ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ይህ ዛሬ ይፋ የሆነው ላውንጅ ለደንበኞች የምንሰጠው አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ መድረሱን ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ለደንበኞች ልዩ እና ምቾት የተሞላበት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

የፕሪሚየር ላውንጅ ለአየር መንገዱ ታላቅ ስኬት እንደሆነ ገልፀው፤ የአፍሪካ ዋና መግቢያ በር የሆነው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያለውን ሚና በእጅጉ ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም