የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአፍሪካ ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአፍሪካ ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአፍሪካ ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ማወጣው መልዕክት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከታኅሳስ 7-8/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉብኝት ያደርጋሉ ብሏል፡፡
ይህም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ሲልም አስታውቋል፡፡
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በሕንድ የአፍሪካ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ የሁሉ አቀፍ ልማትና ስትራቴጂካዊ ትብብር፣ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎላ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ዋነኛ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል መሆኗን ያረጋግጣል ነው ያለው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ከተለመደው የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የአለም አቀፉን የደቡብ ድምጽ በጋራ ለማጉላት ያላት ፍላጎት መጨመሩንም ያሳያል ሲል አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያና ሕንድ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ግንኙነት የጀመሩ ቢሆንም ሀገራቱ ከ2ሺህ ዓመት በላይ የዘለቀ ጥልቅ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ ነው ያለው፡፡
ህንድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በሰፊው ዓለም መካከል እንደ ድልድይ አድርጋ በማስቀመጥ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በመደገፍ ዘላቂ ወዳጅነቷን አሳድጋለች ብሏል፡፡
ሕንድ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘላቂ ልማት ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለማጠናከር ፍላጎቷ ከፍተኛ ነውም ነው ያለው አገልግሎቱ በመልዕክቱ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሀገራቸዉን ቁርጠኝነትን ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል፡፡
ህንድ የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያድግና የጋራ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ አጋዥ የሆነውን የብሪክስ አባል የመሆን ጥያቄ ከደገፉ አባል ሀገራት አንዷ ስትሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሻሻል በትብብር እየሰራች ትገኛለች ሲልም ገልጿል።
ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የሚያደርጉት ውይይትም በዋና ዋና ዘርፎች በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል ትብብር፣ በአቪዬሽን እና በዲጂታል ሽግግሮች ዙሪያ ፍሬያማ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብሏል፡፡
ጉብኝቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነቶች ባለፈ ኢትዮጵያ በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያደገ የመጣውን ተደማጭነቷን የሚያሳይና ከአለማችን 10 ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገራት አንዷ የሆነቸው ሕንድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጋ መቀበሏን ማሳያ ነው ሲልም አስታውቋል፡፡