ፋይዳ መታወቂያ ሴቶችን በኢኮኖሚ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ መታወቂያ ሴቶችን በኢኮኖሚ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡- ፋይዳ መታወቂያ የሴቶችን የዲጂታል ተሳትፎ በማሳደግ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ኢኮኖሚ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለፁ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የሴቶች ንቅናቄና የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
በተለይም ሴቶችን በፋይናንስ ተጠቃሚ በማድረግ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
ፋይዳ ለሴቶች፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች አካታችነት፣ የእኩልነት መብት ማረጋገጫና የማስፈፀሚያ መሳሪያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር የሴቶችን የዲጂታል ተሳትፎ በማሳደግ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ መንግስት ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት መረጋገጥ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው፤ ሌሎች ሥርዓቶችም እርስ በእርስ እንዲተሳሰሩ ተደርጎ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የሴቶችን ዲጂታል ተሳትፎ በማሳደግ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል አገልግሎት እንዲጠቀሙና እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማድረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ በቀጣይ በዞንና ወረዳ ደረጃ ምዝገባ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚዎች 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሀገር እስከ ሰኔ 30 ድረስ የፋይዳ ተጠቃሚዎችን ቁጥር 90 ሚሊየን ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባን ለማሳካት የሴቶች ተሳትፎ ቁልፍ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።