ቀጥታ፡

ታማኝ ግብር ከፋዮች የመዲናዋን ተወዳዳሪነት በማሳደግ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-ታማኝ ግብር ከፋዮች የመዲናዋን ተወዳዳሪነት በማሳደግና ዜጎችን በልማት ተጠቃሚ በማድረግ አሻራቸውን እያሳረፉ  መሆኑ ተመላከተ፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከፕላቲኒየም እና ወርቅ ደረጃ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡


 

በቢሮው እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክቶ ሰነድ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ገቢዎች ምክትል ቢሮ ኃላፊ መሐመድ አብዱራህማን፤ቢሮው በርካታ የአሰራር ማሻሻያ ጥናቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል፡፡

በመደበኛ የታክስ ኦዲትና በቅድመ ኦዲት ስራ ላይ ለውሳኔ አሻሚ የሆኑና ለብልሹ አሰራር በር ከፍተው የነበሩ አሰራሮችን በመፈተሸ ማስተካከል መቻሉንም ተናግረዋል፡፡


 

ከአደረጃጀት አኳያም ለቢሮው አሰራር አጋዥ የሆኑ አዳዲስ አደረጃጀቶችን ወደ ስራ የማስገባት ሂደት መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ግብር ከፋዮች ያቀረቡትን መረጃ በማጣራትም ብልሹ አሰራር በፈጸሙ ሠራተኞች እና አመራሮች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዱን ጠቅሰዋል።

የወርሃዊ ቫት አሰባሰብ የማሳወቂያ መርኃ ግብረ በማውጣትና አሰራሩን በማዘመን የግብር ከፋዮችን እንግልት የሚያስቀሩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ግብር ከፋዮች በሰጡት አስተያየት፤ ቢሮው አገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘመነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ያለ ደረሰኝ በሚደረጉ ግብይቶች ላይ ተጨማሪ ቁጥጥሮችን የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡


 

በሌላ በኩል ቢሮው የሚያወጣቸው የአሠራር መመሪያዎች በፍጥነት ሊደርሱን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በዚሁ ወቅት፤ ቢሮው ያለደረሰኝ የሚደረጉ ግብይቶችን ለመቆጣጠር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

መርካቶ አካባቢ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ በቁጥጥር ላይ ብቻ እንዲሠሩ መደረጉን ጠቁመው በዚህም ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸውን ህጎችና መመሪያዎች በማህበራዊ ሚዲያዎችና በቢሮው ድረገጽ ላይ ለግብር ከፋዮች ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን፤ ከግብር ከፋዮች በተሰበሰበ ገቢ የከተማዋን ተወዳዳሪነት ለማሣደግና የዜጎችን ሕይወት ከማሻሻል አኳያ ትርጉም ያለው ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም ታማኝ ግብር ከፋዮች በመዲናዋ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ውስጥ አሻራቸውን እያሳረፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፍትሐዊነት እና ግልጽነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በከተማ ደረጃ 350 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን በማንሳት፥ ግብይቶችን ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ ለፕላቲኒየም እና ለወርቅ ደረጃ የግብር ከፋዮች የልዩ ተጠቃሚ ካርድ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም