የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-በጤናው ዘርፍ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርታማነትንና አቅርቦትን ከማሳደግ አኳያ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመድሃኒት ምርቶችን ስርጭት ለመከላከል የተዘጋጀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት የግዥ ስርዓቶችን በማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን ምርት የገበያ ድርሻ ከስምንት በመቶ ወደ አርባ ሁለት በመቶ ማድረስ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ከደረጃ በታች ወይም ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶችን ለመቀነስ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስርዓት ተዘርግቶ የቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የቁጥጥርና የአቅርቦት ስርዓቱ በጤናው ዘርፍ ዕቅድ መሰረት በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ስራዎች መሰራታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
የቁጥጥር ስርዓቱን ለማጠናከር በተሰራው ስራ ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የኤም ኤል 3 ደረጃ (Maturity Level 3) ማግኘቷ ትልቁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ስትራቴጂ ይፋ መደረግ ከደረጃ በታች ወይም ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶችን የመከላከል፣ ጥራት፣ ደህንነት እና ፈዋሽነት የጎደላቸው መድኃኒቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ መከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስትራቴጂው የዲጂታል ቴክኖሎጂን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ራሱን የቻለ አሰራርና አደረጃጀት እንደሚፈጥር እና የቁጥጥርና አቅርቦት አቅምን እንደሚያጠናክርም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ በበኩላቸው፤ መድኃኒቶች ለህዝብ ከመቅረባቸው በፊትም ሆነ ከቀረቡ በኋላ የጥራት፣ የደህንነት እና የፈዋሽነት ደረጃቸውን ማሟላት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሆኖም ከደረጃ በታች እና ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶች በጤናው ዘርፍ ውስጥ በቁጥጥር እና አቅርቦት ሰንሰለት ላይ እንቅፋት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ይህን ተግዳሮት ለማቃለል በሀገር ውስጥ የቁጥጥር ዘርፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ የቁጥጥር ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በመደረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስትራቴጂው ችግሩን ለማቃለል ትልቅ አቅም እንደሚሆን አንስተው፤ የሁሉንም ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት አስተዋፅኦ ስለሚጠይቅ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ገልጸዋል።