የኢትዮጵያ እና የህንድ ዘመን አይሽሬ እና ድንበር ተሻጋሪ ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የህንድ ዘመን አይሽሬ እና ድንበር ተሻጋሪ ወዳጅነት
በሙሴ መለስ (ኢዜአ)
ኢትዮጵያ እና ህንድ ረጅም ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አላቸው። በዚህም የስልጣኔ እሴቶችን ይጋራሉ።
ሁለቱ ሀገራት የንግድ ትስስር ከፈጠሩ ከ2000 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ እና ህንድ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሰረት የሀገራቱ ታሪካዊ ወዳሽነት እንደሆነም ይወሳል።
ኢትዮጵያ እና ህንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1948 ነው።
እ.አ.አ በ1950 ሳርዳት ሳንት ሲንግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የህንድ አምባሳደር በመሆን ተሹመዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ እና ህንድ በየሀገራቱ ኤምባሲ በመክፈት የዲፕሎማሲ ትብብሩን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ገልጸዋል።
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እ.አ.አ በ1956 እና በ1958 በህንድ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ከኢትዮጵያ መሪዎች ጉብኝቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
እ.አ.አ 1960 ዎቹ ማብቂያ እና 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የህንድ ፕሬዝዳንቶች የነበሩት ሳርቬፓሊ ራድሃክሪሽናን እና ዛኪር ሁሴን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝቶችን አድርገዋል።
እ.አ.አ በ2011 ከአንድ ዓመት በፊት ህይታቸው ያለፈው የቀድሞው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ በኢትዮጵያ ያደረጉት የስራ ጉብኝትም ተጠቃሽ ነው።
የቀድሞው የህንድ ፕሬዝዳንት ራም ናት ኮቪንድ እ.አ.አ በ2017 የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ በጉብኝታቸው ህንድ እና ኢትዮጵያ በንግድ፣ ኮሙኒኬሽን እና የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ የጋራ መግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2023 ባዘጋጀችው 15ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከነበራቸው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
የሀገራቱ መሪዎች በወቅቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ የወጣቶች ክህሎት ማጎልበት እና በሕዝብ ለሕዝብ ልውውጥ ዙሪያ ትብብርን በማጠናከር ዙሪያ ተወያይተዋል።
በወቅቱ ህንድ ባዘጋጀችው የሁለተኛው “Voice of Global South Summit” በተሰኘው ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተሳትፎ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2016 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንደራ ሞዲ በህንድ አጠቃላይ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈውም ነበር።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንደራ ሞዲም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን የደስታ መግለጫ መልዕክት በመቀበል በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት እንደሚያድግ መግለጻቸውም ይታወሳል።
ህንድ እና ኢትዮጵያ በአፍሪካና በደቡብ ደቡብ ትብብር ያላቸውን አጋርነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በዚህም ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት የሁለትዮሽ ትብብር ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ያስታወቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 20ኛው የቡድን 20 አባላት ሀገራት ጉባኤ ከነበራቸው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ትርጉም ያለው እና ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ህንድ የቡድን 20 አባል ሀገር መሆኗ የሀገራቱን የባለብዙ ወገን ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር ነው።
ከእ.አ.አ 2021 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ሀገራቱ የሁለትዮሽ እና የባለዙወገን ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል።
በወቅቱ የህንድ የትምህርት፣ ንግድ፣ ልማት፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሀገራቱ ግንኙነት የበለጠ እየጠነከረ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው።
ህንድ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ድጋፍ ያደረገች ሲሆን በብዝሃ ወገን ማዕቀፉ ሁለቱ ሀገራት በትብብር እየሰሩም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ እና ህንድ በተለያዩ ጊዜያት በአየር ትራንስፖርት፣ ኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት፣ መከላከያ፣ ተደራራቢ ታክስን የማስቀረት፣ ንግድ፣ ኮሙኒኬሽን ሳይንስ፣ባህል፣ ትምህርት እና የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ማቋቋምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መስራት የሚያስችሏቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
እ.አ.አ ፌብሩዋሪ 2025 ኢትዮጵያ እና ህንድ በመከላከያና ደህንነት ዘርፍ የተፈራረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት ቁልፍ የሚባል ነው።
እ.አ.አ በ2023/24 በወጣ መረጃ የኢትዮጵያ እና ህንድ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ምጣኔ 271 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።
ኢትዮጵያ አተር፣ ቅመማ ቅመሞች፣ የቆዳ ውጤቶች እና የከበሩ ድንጋዮችን ወደ ህንድ ትልካለች።
ከህንድ ደግሞ ማሽነሪዎች፣ የመድኃኒትት ምርቶች እና የብረታ ብረት ውጤቶችን በዋናነት ታስገባለች።
ህንድ የኢትዮጵያ ዋንኛ የኢንቨስትመንት አጋር ከሚባሉ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች። ከ500 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅ፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
ህንድ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ታደርጋለች።
ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ ጤና እና መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሁለቱ ሀገራት አበይት የትብብር መስኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሞዲ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከማንሞሃን ሲንግ በኋላ ኢትዮጵያን የጎበኙ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ህንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት ማሳደግን ያለመ ነው።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በፓርላማ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያሳያል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ተከታታይ የሁለትዮሽ ውይይቶች እና የጉብኝት ልውውጦች የኢትዮጵያ እና የህንድን ግንኙነት የበለጠ የሚያጸኑ ናቸው።
ኢትዮጵያ እና ህንድ በታዳሽ ኃይል፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ግብርና ማቀነባበሪያን ጨምሮ በአዳዲስ መስኮች ትብብራቸውን የማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላቸው።
የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከእርስ በእርስ ግንኙነት ባለፈ የአፍሪካ እና ህንድ እንዲሁም የደቡብ ደቡብ ትብብር ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።
ከ2000 ዓመት በፊት የተጀመረው የሀገራቱ ወዳጅነት ወደ ጠንካራ እና ጽኑ ትብብር ተቀይሯል። በማይናወጥ መሰረት ላይም ቆሟል።
የበለጠ ጥልቀቱ እየጨመረ የመጣው የሀገራቱ ግንኙነት በጋራ ብልጽግና፣ ስትራቴጂካዊ ትስስር፣ ዘላቂ ልማት እና የሀገራቱን ዜጎች ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ አጠናክሮ ለመቀጠል የጋራ ቁርጠኝነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል።