ቀጥታ፡

ስልጠናው አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማቀላጠፍ አቅም ይፈጥርልናል

ባሕር ዳር፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-በመደመር መንግስት መሰረታዊ ሃሳቦችና መዳረሻ ግቦች ዙሪያ እየተሰጡ ያሉ ስልጠናዎች   ሕብረተሰቡን   ይበልጥ ለማገልገል  አቅም  እንደሚፈጥርላቸው የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር  የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

በባሕርዳር የአቅም ግንባታ ስልጠናው ላይ እየተሳተፉ ካሉ የመንግሰት ሰራተኞች መካከል  የምስራች አበጀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስልጠናው  የመንግስት ሰራተኛውን የመፈጸም አቅም በማላቅ  አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ አቅም የሚሆን ነው።


 

የመደመር መንግስት እሳቤና እይታዎችን  ጠንቅቆ መገንዘብ  ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት  እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ስልጠናው የመደመር መንግስት እይታዎችን ተረድተው በመተግበር በሚሰጡት አገልግሎት የሕብረተሰቡን እርካታ በላቀ ብቃት ለማረጋገጥ ያግዛል ያሉት ደግሞ  መልካሙ አለባቸው ናቸው።


 

የግብርናም ሆነ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ማሳካት የሚቻለው ለሕብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደር ማስፈን ሲቻል እንደሆነ  መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም የሰራተኛውን ግንዛቤ በማሳደግ በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚተጉ ገልጸዋል።

ስልጠናው የመደመር መንግስት እይታና እሳቤዎችን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ እንድንረባረብ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥርልናል ብለዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአቅም ግንባታና ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጊዜው ታከለ በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ ስልጠናው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነውን ግብርና ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የመንግስት ሰራተኛው የጎላ ሚናውን እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።


 

ለዚህም የመንግስት ሰራተኛው የመደመር መንግስት ግቦችን የጋራ በማድረግ ለተፈጻሚነታቸው ይበልጥ መትጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም