ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሴቶች አደረጃጀቶች ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር አለበት

ደብረ ብርሀን፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል  ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሴቶች አደረጃጀቶች  ተሳትፎ  ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ደነባ ከተማ ከሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በሰላም፣ በልማትና መልካም አስተዳደር  ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ መድረክ የተገኙት ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት ፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሲደረግ በቆየው እንቅስቃሴ  የሴቶች አደረጃጀቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።


 

ይህንን ይበልጥ በማጎልበት ሴቶች የፎረምና የልማት አደረጃጀቶቻቸውን  በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም ጠንክረው ከመስራት ባለፈ በመረዳዳት ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ሴቶች ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ  መሆኑንም  አክለዋል።

በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ሕዝብና አስተዳደር በ7 ሚሊየን ብር አረጋዊያንን ለመደገፍ የተገነባው የገቢ ማስገኛ ህንፃ ለሌሎች ወረዳዎች ጭምር ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ  ዘላለም አረጋ ፤  በክልሉ የሴቶችን  ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሴቶችን ተጠቃሚነትና  ተሳትፎ  ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም መስፈን አስገዳጅ በመሆኑ ለዚህም ሴቶች ሲያበረክቱት የቆዩትን አስተዋጽኦ   እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በዞኑ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ  ተክለየስ በለጠ ናቸው፤።

ሴቶች በግብርና እና በንግድ  ዘርፍ ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲሆኑም እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ  ተፈሪ በሱፍቃድ እንዳሉት፤ ሴቶች በዘላቂ ሰላም ማስፈን ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ ከማጠናከሩ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።

የመድረኩ ተሳታፊ  ሚሚ በቀለ፤ በሴቶች አደረጃጀት የእህል ወፍጮ ቤት  ከፍተው በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለሰላም ግንባታ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች  እንዲስፋፉ ከመንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ   ራሄል ይግዛው ናችው።


 

በመድረኩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የሴት አደረጃጀቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም