በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ያዘጋጀው የመጀመሪያው የቱሪዝም ፎረም በአራዳ ፓርክ ተካሂዷል፡፡
ፎረሙ በዋናነት ዜጎች በመዲናዋ ስላሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና የጉብኝት ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በቱሪዝም ሚኒስቴር ስትራቴጂክ አማካሪ የሆኑት ቴዎድሮስ ደርበው፤ ፎረሙ በዋናነት የመዲናዋን ጸጋዎች ለማስተዋወቅና የዘርፉን ባለድርሻ አካላት በአካል በማገናኘት ተሞክሮ እንዲለዋወጡና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች እንዲበራከቱና የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲስፋፉ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ በበኩላቸው፤ ፎረሙ በዋናነት በከተማዋ የቱሪዝም እድገት ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ፎረሙ በተለይም ከተማዋን በሚገባት ልክ ለማስተዋወቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጠቃሚ ግብአቶችን አግኝተንበታል ብለዋል፡፡
በፎረሙ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ፎረሙ የእርስ በርስ ትስስርን ለማጠናከር እና ተሞክሮን ለመለዋወጥ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አስቴር ሰለሞን፤ ፎረሙ ባለድርሻ አካላት ስለ ዘርፉ አቅምና ቀጣይ ሥራዎች የጋራ ግንዛቤ የፈጠሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሼፎች አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ሼፍ ሄኖክ ዘሪሁን በበኩሉ፤ ፎረሙ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻዎች ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሷል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችንና ክፍተቶችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር የቦርድ አባል ናሆም አድማሱ ናቸው ፡፡
በመድረኩ የዘርፉ ተዋናዮች የተሳተፉባቸው የቱሪዝም ንግድ አውደ ርዕይ፣ ኤግዝቢሽንና የፎቶ አውደ ርዕይ ተካሂዷል፡፡