ቀጥታ፡

የ2018 ዓ.ም የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የውድድር ዘመን ዛሬ በይፋ ተጀመረ   

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦ የቱሪዝም ዘርፉን የማስተዋወቅ አላማ ያለው የ2018 ዓ.ም የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ የውድድር መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ሆኗል። 

የውድድር መርሃ ግብሩ ዘንድሮ የደብረ ብርሃን እና ሐረር ከተሞችን አካቷል። 

ይህ ስፖርት እና ቱሪዝምን በማቀናጀት የኢትዮጵያን ከተሞች እና የቱሪዝም ስፍራዎችን በስፋት እያስተዋወቀ የሚገኘው መርሃ ግብር አዳዲስ ከተሞችን በመጨመር ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የሚካሔድ ሲሆን ከጥር እስከ ሐምሌ ፤ ከአንኮበር እስከ ሐረር በር በመሪ ሀሳብ ይከናወናል። 

ልወቅሽ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ትውልዱ ስለ ሀገሩ ባህል፣ ታሪክ እና የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲያውቅ ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ ነው።

ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተለያዩ ከተሞች የ"ልወቅሽ ኢትዮጵያ" የሩጫ ውድድር ባለፉት ዓመታት እየተካሄደ ይገኛል። 

ዘንድሮም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ በሚል ስያሜ በስድስት የክልል ከተማዎች ላይ ተከታታይ የሩጫ ውድድር  እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል። 


 

በ2017 ዓ.ም በአራት  መዳረሻ ከተማዎች ላይ የተካሄደው የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ተከታታይ ውድድር ፤ በዚህም ዓመት ደብረብርሃን እና ሐረርን በመጨመር ስድስት ከተማዎች ላይ ይካሄዳል። 

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈውም ዓመት አዘጋጅ በነበሩት ሃዋሳ፣ ጅማ፣ በቆጂ እና አርባምንጭ ላይ ለተከታታይ ዓመታት ያደረገ ሲሆን ዘንድሮም ውድድሩን ለማካሄድ ተዘጋጅቷል። 

የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስፖርት እና ቱሪዝምን በማስተሳሰር እየሰሯቸው ያሉትን ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ለመስራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል። 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ልወቅሽ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያንን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሀገራት ተሳታፊዎችን መሳብ የቻለ ዝግጅት ለመሆን መብቃቱን ገልጸዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ  መኪዩ መሃመድ በበኩላቸው “ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር በማጣመር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል። 

መንግስት ልወቅሽ ኢትዮጵያ ውድድር እንዲሰፋ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል። 


 

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ በበኩላቸው፤  ‘ልወቅሽ ኢትዮጵያ’ የሚል አዲስ የቱሪዝም ምርት በማስተዋወቃችን እና ከሩጫ ውድድርነት ባሻገር ኢትዮጵያን በትንሹም ቢሆን ማሳየት በመቻላችን ደስተኞች ነን ሲሉ ገልጸዋል።  

መንግስት ንቅናቄው እና ውድድሩ እንዲሳካ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። 

የልወቅሽ ኢትዮጵያ በደብረ ብርሃን ከተማ ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የማራቶን ዱላ ቅብብል እና የሀገር አቋራጭ ውድድሮችን በማካተት ጅማሮውን ያደርጋል።

መርሃ ግብሩ ከሩጫው ባሻገር ልዩ የጉብኝት ፓኬጆችን በማዘጋጀት ዜጎች የተፈጥሮና የቅርስ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ እያስቻለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም