ቀጥታ፡

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመናዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ዘመናዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የትራንስፖርት አገልግሎትን ማዘመን፣ የመንገድ ደህንነትን ማስጠበቅና የትራፊክ አደጋን መከላከል ላይ አሠራርን በማዘመን ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል በኩል እንዲሁም የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥን ከመፈተሽ አንጻር ምን አየተሠራ ነው ሲሉም ጠይቀዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋና የመንገድ ደህንነት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።

በሀገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥር አነስተኛ የሚባል ቢሆንም የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የአሽከርካሪዎች የችሎታ ማነስ እና ስነ-ምግባር ችግር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አብዛኛው የትራፊክ አደጋዎች በአሽከርካሪዎች ስህተት የሚደርሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታትም ትኩረታችንን በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ አድርገናል ነው ያሉት።


 

ለአብነትም የአሽከርካሪዎችን ስነ-ምግባር፣ ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ የስልጠና መስፈርቶችና የብቃት መመዘኛዎች መዘጋጀታቸውን በማንሳት።

በህገወጥ መንገድ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ፍተሻና የመንጃ ፍቃድ በሚሰጡ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትራንሰፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ለአብነትም በወጪና ገቢ ንግድ፣ በህዝብ ትራንስፖርትና በሰሌዳ አሰጣጥ ላይ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን አመልክተዋል።

በትራንስፖርት ዘርፉ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም እንደ ሀገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም