በእውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታችንን እንወጣለን- የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በእውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታችንን እንወጣለን- የመንግስት ሰራተኞች
ጎንደር ፤ ታሕሳስ 7/2018(ኢዜአ) ፡- በእውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡
"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች ውስጥ መልካሙ አበራ እንደተናገሩት፤ የመደመር መንግስት እሳቤ የሲቪል ሰርቪስ የአገልግሎት አሰጣጥ ወቅቱን የዋጀ ቀልጣፋና ዘመናዊነት የተላበሰ እንዲሆን ትኩረት የሰጠ ነው፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱት የመንግስት ሰራተኛው በተመደበበት የስራ መስክ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝብ ሲያገለግል በመሆኑ ይህንን በመተግበር ለተሻለ ለወጥ ሃላፊነቴን እወጣለሁ ብለዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛው በላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እራሱን በማብቃት የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂን መሰረት ያደረገ ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚገባው ከስልጠናው ግንዛቤ መጨበጣቸውን የገለጹት ደግሞ ማሩ መኳንንት ናቸው፡፡
የመደመር መንግስት እሳቤ ለዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መጠናከር ትኩረት የሰጠ ከመሆኑም በላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ችግር ፈቺ የአሰራር መርህ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመደቡበት የስራ መስክ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን በተላበሰ መንገድ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ እርካታን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛው የዲጂታል እውቀትና ክህሎቱ ከፍ እንዲል መንግስት በስልጠና ማብቃቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ ስልጠናው የመንግስትን የቀጣይ አቅጣጫዎች ተገንዝበን ለተግባራዊነቱ ዝግጁ እንድንሆን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ ነጻነት መንግስቴ በበኩላቸው፤ ስልጠናው የተመቻቸው ሰራተኛው የመደመር መንግስት እይታና እሳቤዎችን በሚገባ ተገንዝቦ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የመንግስት ሰራተኞች እየተሳተፉ ነው፡፡