ኢንስቲትዩቱ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ኦዲት አሠራር የሚያዘምን ሥርዓት ሊዘረጋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ኦዲት አሠራር የሚያዘምን ሥርዓት ሊዘረጋ ነው
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የፋይናንሺያል ኦዲት አሠራር ይበልጥ ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ሊዘረጋ ነው።
የፋይናንሺያል ኦዲት ሥርዓትን በዲጂታል ማዘመን ለኦዲት ጥራት መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ፋይናንሺያል ኦዲት ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ሥምምነት ተፈራርሟል።
ሥምምነቱን የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ተፈራርመዋል።
በሥምምነቱ መሰረት ኢንስቲትዩቱ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱን የፋይናንሺያል ኦዲት ሥርዓት ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግር የቴክኖሎጂ ሥርዓት የሚዘረጋ ይሆናል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት የመንግሥት ተቋማት አሠራራቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተርም ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ አሠራርን ለመተግበር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር የፋይናንሺያል ኦዲትን ለማዘመን የተደረገው ሥምምነት የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ተቋማት የሚበጀትላቸውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውን ኦዲት ማድረግ የሚያስችለው የፋይናንሺያል ኦዲት ሥርዓትን ማዘመን ለኦዲት ጥራት መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
አሠራሩን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ጊዜንና ገንዘብን መቆጠብ እንደሚያስችል አመልክተው እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥርያ ቤትን የፋይናንሺያል ኦዲት አሠራርን ዘመናዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም የፋይናንሺል ኦዲት የሚከወንባቸው መንገዶች እና አጠቃላይ ይዘት ላይ አስፈላጊው ጥናት መደረጉን ጠቁመው የጥናት ውጤቱን መሰረት በማድረግ አሠራሩን የሚያዘምኑ ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።
ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ የዲጂታል ሥርዓቱን የማበልጸግ ሥራ እንደሚያጠናቅቅ አመልክተዋል።