ቀጥታ፡

በግመል ጤንነት፣ እንክብካቤና ደህንነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሰመራ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡- በግመል ጤንነት፣ እንክብካቤና ደህንነት ላይ ያተኮረ  የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ ይፋ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ግብርና ኮሌጅ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ሲሆን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የግመል ጤንነት፣ እንክብካቤና ደህንነት ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚተገበር መሆኑም ታውቋል።


 

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የሰመራ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ዓሊ እንደተናገሩት፤ የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

በግመል ላይ ያተኮሩ መሰል ፕሮጀክቶች ብዙም ያልተለመዱ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አደም፤ የአሁኑ ፕሮጀክት ግን በዓይነቱ ልዩ የሆነና የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሠረት በሆነው በግመሎች ጤንነትና  ምርታማነት ላይ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ በአምስት ዓመት ትግበራ 16 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት መሆኑንም አክለዋል።


 

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይና በዩኒቨርሲቲው የእንሰሳት ህክምናና ግብርና ኮሌጅ ዲን ሂካ ዋቆቶላ (ዶ/ር) ፤ፕሮጀክቱ የግመል ህክምና፣ እንክብካቤና የአረባብ ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ በተለይም የአርብቶ አደሩ ህይወት መሻሻል አስተዋፅኦ ለማድረግ ታልሞ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሀገሪቷ የጋማ ከብቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በበረሃው አካባቢ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለውና የአርብቶ አደሩ መገለጫ በሆነው በግመል ላይ ግን በቂ ስራ አለመሰራቱን አንስተዋል።

ይህን ለመቅረፍ ፕሮጀክቱ በሐሳብ ደረጃ ምርምር ሲደረግበት ለረጅም ጊዜ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።

በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን ለተጀመረው ፕሮጀክት ውጤታማነት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የሚያስፈጽሙት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም