ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል ህዝብ በተሟላ መንገድ በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ አለበት-የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

መቀለ፤ ታህሳስ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል ህዝብ እንደ ሌሎች ክልሎች ህዝቦች በተሟላ መንገድ በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ አለበት ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲካሄድና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

በእስካሁኑ ሂደትም በ11 ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ ተደርጎ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ በማከናወን የምክክር ሂደቱ በወሳኝ የስኬት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ኢዜአ በመቀሌ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች እንዳመለከቱት፣ በሀገራዊ ምክክር ታሪካዊ ሁነት ላይ የትግራይ ክልል ህዝብ በተሟላ መልኩ በመሳተፍ አጀንዳውን እንዲያቀርብና በሀገሩ ጉዳይ እንዲመክር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ የቅድመ ምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ህዝቡ በየደረጃው በምክክሩ የተሟላ ተሳትፎ እንዲኖረው መስራት እንዳለበትም ገልፀዋል።


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ አቶ ካህሳይ ግደይ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታትና የግጭትና ጦርነትን አዙሪት መቋጨት የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፣ የትግራይ ህዝብ አሉኝ የሚላቸውን አጀንዳዎች አቅርቦ ለመመካከር ታሪካዊ አጋጣሚውን መጠቀም አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለዘመናት የነበሩ የግጭትና ጦርነት አዙሪቶች በየትውልዱ ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ መሆኑን አስታውሰው፤ ተመካክረን ችግሮችን እንፍታ በማለት የተጀመረው ጥረት ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም የትግራይ ክልል ህዝብ የዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብዙ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ እናውቃለን፣ እድሉን ማንም ወገን ሊያመክነው አይገባም፣ አጋጣሚውን ልንጠቀምበት ግድ ይላል ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ብርሃነ ገብረስላሰ፤ የሀገርን መሰረታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከመመካከር በላይ መፍትሄ ሊኖር እንደማይችል ተናግሯል።


 

በመሆኑም የግጭትና ጦርነትን ምእራፍ በመዝጋት ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገር ለመገንባት ዛሬ ላይ መምከር የግድ ይለናል ብሏል።

በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ የትግራይ ክልል ህዝብም የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን አለበት ሲል ተናግሯል።

የትግራይ ክልል ህዝብ አሁን ላይ ከምንም በላይ ሰላምንና ልማትን ይሻል ያለው ብርሃነ፤ በምክክር ችግሮቻችንን ለመፍታት ሁላችንም ሃላፊነት ወስደን ማገዝ፣ መተባበርና መስራት ይጠበቅብናል ብሏል።


 

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚድያና ኮሚኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ግርማ ሞገስ፤ የክልሉ ህዝብ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚኖረውን ሚና ለማጠናከር የምክከሩ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት አንስተው ለዚህም ኮሚሽኑ እድሎችን እያመቻቸና እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ በሀገሪቷ የቆዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ስብራቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ በገለልተኝነት አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ዜጎች በጋራ እንዲመክሩ ማመቻቸት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም