ኢዜማ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው በሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ተሳትፎ ዝግጅትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢዜማ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መርህ ምርጫ ላይ በመሳተፍ መንግሥት ለመሆን የሚሰራ ፓርቲ ነው።
በዚህም ፓርቲው በቀረፃቸው ፕሮግራሞች መሠረት ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት መከበር ፋይዳ ባላቸው ለሀገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኢዜማ ምርጫን የዴሞክራሲ ግንባታ ቁልፍ መሳሪያ አድርጎ ይወስዳል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ በህዝብ ድምጽ ቅቡልነት ያለው መንግስት መመስረት የሚቻልበት መሆኑንም አንስተዋል።
ለሀገር ጥቅምና ፍላጎት መሳካት በትብብር መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መተባበር፣ በልዩነቶች ላይ መመካከር ፓርቲው ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢዜማ በነፃ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ የምርጫ ሂደት በመሳተፉ መንግስት ለመሆን የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሰላማዊ አማራጭ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴም ለሀገር እንደማይጠቅም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ኢዮብ መሳፍንት፤ ምርጫ የፖሊሲ አማራጭ ማቅረቢያና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማጽኛ ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ኢዜማ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰባተኛው ምርጫ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብን ድምጽ ማግኘት የሚያስችል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል።
በዚህም ሀገራዊ ምርጫውን ማካሄድ በሚቻልባቸው አስቻይ ሁኔታዎችና አካባቢዎች ሁሉ ኢዜማ እንደሚሳተፍ አረጋግጠዋል።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እዮኤል ሰለሞን፥ ባለፉት ዓመታት ቀጣይ በሚካሄደው ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ኢዜማ በምርጫው የሚሳተፈው ሀሳብን ለሕዝብ በማድረስ ትክክለኛ አማራጭ ሆኖ ለመገኘትና ምርጫውን ለማሸነፍ በማለም መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ምርጫን ከፓርቲ በዘለለ በአጠቃላይ ያለውን ጠቀሜታ በጥልቀት በማየት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለስኬታማነቱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
መንግሥት፣ ገዢው ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ምርጫ ቦርድ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ መራጩ ሕዝብና ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ ግልፅነት፣ ዲሞክራሲያዊነትና ስኬታማነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድ መዳበር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫን ሊከተሉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።