ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተመሳስለው የተመረቱ መድሃኒቶችን ስርጭት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ አጋርነት ወሳኝ ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተመሳስለው የተመረቱ መድሃኒቶችን ስርጭት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ አጋርነት ወሳኝ ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ):-ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተመሳስለው የተመረቱ መድሃኒቶችን ስርጭት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተጠናከረ አጋርነት ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመድሃኒት ምርቶችን ስርጭት ለመከላከል የተዘጋጀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ መንግሥት ከህዝብና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባከናወናቸው ተግባራት በሁሉም የጤና አገልግሎት መስኮች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ከበሽታ መከላከል በተጨማሪ አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ያደረገው አዲሱ የጤና ፖሊሲ ወደ ትግበራ ገብቶ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም፥ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት እያደገ እና እየተስፋፋ ቢሆንም፥ ጥራት፣ ደህንነት እና ፈዋሽነት የጎደላቸው መድኃኒቶች በገበያ ላይ እንዳይቀርቡ የመከላከል፣ የመለየት እና ምላሽ የመስጠት ስርዓቱን ማጠናከር ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቁጥጥር እና የአቅርቦት ስርዓቱ እንዲዘምንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ አዳዲስ ስርዓቶችን ለመተግበር በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ይፋ የሆነው ከደረጃ በታች ወይም ተመሳስለው የተመረቱ መድኃኒቶችን የመከላከል፣ የመለየት እና ምላሽ የመስጠት ስትራቴጂ፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማጣራትና ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስትራቴጂው ራሱን የቻለ አሰራር እና አደረጃጀት የሚፈጥር፣ የቁጥጥርና አቅርቦት አቅምን የሚያጠናክር እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን የሚያቀናጅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ በበኩላቸው፥ የመድሃኒት ቁጥጥር ዘርፍን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፥ በዚህም ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ደረጃቸውን ያልጠበቁና ተመሳስለው የተመረቱ መድሃኒቶችን ለመከላከል የተዘጋጀው አዲሱ ስትራቴጂ የህብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት መረባረብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።