ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች በዘላቂነት ተፈትተው ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻችንን እንወጣለን - የሀገር ሽማግሌዎች

ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 7/2018(ኢዜአ):- በሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች በዘላቂነት ተፈትተው ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የሚዛን አማን ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ የቆዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ስብራቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን በገለልተኝነት አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ዜጎች እንዲመክሩ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም እስካሁን በ11 ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለይቶ አጀንዳቸውን በመቀበል የምክክር ሂደቱ ቀጥሏል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ በሚዛን አማን ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌዎች ተመካክሮ ችግሮችን ከመፍታት የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ገልጸዋል።

በመሆኑም በሀገር ጉዳይ በቅንነት ተቀራርቦ በጋራ በመምከር ለትውልዶች የምትመች፣ ሰላም የሰፈነባትና ከድህነት የተላቀቀች ሀገር መገንባት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በዚህም በሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች በዘላቂነት ተፈትተው ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል ሊቀ ሀገር ሀብተማርያም ካዝንቴት፤ ከዝግጅት ምእራፍ ጀምሮ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የአመታት ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን የሀገር ሽማግሌዎች ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት መጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን አንስተው፥ ለስኬቱ የሁላችንም እገዛና ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ሙሉጌታ ተስፋዬ፤ የሀገር ሰላም የሚጸናውና ልማት የሚረጋገጠው በመመካከር፣ በመግባባትና የጋራ ዓላማ ሰንቆ መስራት ሲቻል መሆኑን ገልጸው፥ የምክክሩን እድል ለፍሬ ማብቃትና ለሀገር መስራት አለብን ብለዋል።

በምክክሩ የእስካሁኑ ሂደት በአሳታፊነቱና አካታችነቱ የብዙዎችን ጥያቄ ያደመጠ እና አጀንዳቸውን ያስተናገደ መሆኑን አንስተው፥ መፈትሄ በሚያመጣ መልኩ መቋጨት አስፈላጊ ስለመሆኑ አጽኖት ሰጥተዋል።

የሀገር ሽማግሌ አበራ ደስታ በበኩላቸው፥ ለነገ ትውልድ ምቹ፣ የተረጋጋችና አንድነቷ የጸና ሀገርን ለማስረከብ ተስፋ ለተጣለበት የምክክር ሂደት ስኬት የጋራ ሃላፊነታችን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በይፋ ከተቋቋመ ጀምሮ ከዝግጅት ምእራፍ ጀምሮ በምክክር ምእራፍ እስካሁን በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም