ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እድሎችን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓ የኢንቨስትመንት ፍሰቷን ያሳድጋል-የሩዋንዳ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃፔሎ ቲሺኦል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እድሎችን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓ የኢንቨስትመንት ፍሰቷን ያሳድጋል-የሩዋንዳ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃፔሎ ቲሺኦል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እድሎችን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ እንደሚያስችላት የሩዋንዳ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃፔሎ ቲሺኦል ገለጹ።
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በትክክለኛ መንገድ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን በጥር ወር 2017 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አካል ነው።ገበያውን የሚቆጣጠር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
የሩዋንዳ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃፔሎ ቲሺኦል፥ የካፒታል ካበያን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን ለውጭ ክፍት ማድረጓ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
የውጭ ባለሀብቶች በካፒታል ገበያ ላይ መሳተፋቸው በመዋዕለ ሰነድ ገበያው የሚገኘውን ካፒታል ለኢኮኖሚ እድገት ለመጠቀም እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አድማስ እና እድሎችን በማስፋት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት እና ልማት መሰረት እንደሆነም ነው የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው።
ኩባንያዎች ወይም ተቋማት ወደ ገበያው በመምጣት ከሰነደ መዋዕለ ገበያው የአክሲዮን ግዢ መፈጸም እና መሸጥን ጨምሮ የተለያዩ ካፒታል ማግኛ አማራጮችን መጠቀማቸው ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያዋን የመለወጥ እና ለውጭ ክፍት የማድረግ ተግባር ጠንካራ መሰረት ከመጣል ባለፈ ኩባንያዎች ወደ ገበያው እንዲመጡ በማድረግ ዘርፉ እንዲያድግ እንደሚያስችል ነው ያብራሩት።
በዚህ ረገድ የካፒታል ገበያውን ክፍት የማድረግ የፖሊሲ እርምጃ ገበያውን የበለጠ እንዲሰፋ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
በካፒታል ገበያው ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ዓለም አቀፍ አሰራርን መከተል እና በዘርፉ ካሉ ተቋማት ልምድ መቅሰም እንደሚገባ ገልጸው፥ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ያላት ጅማሮ መልካም የሚባል እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ምቹ ምህዳር መፈጠሩ በርካታ ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሚያግዝ እና ይህም ለኢኮኖሚ እድገት በጎ ተጽእኖ እንደሚኖረው ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፣ በአፍሪካም ትልቅ የኢኮኖሚ ኃይል የመሆን አቅም አላት ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ትሩፋቶች ባጠረ ጊዜ እንደምታገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛል።