በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰፈነው ሰላም በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰፈነው ሰላም በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሰቆጣ፤ ታሕሳስ 7/2018(ኢዜአ)፡ - በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሰፈነው ሰላም በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ገለጸ።
አስተዳደሩ ከደሃና ወረዳ እና የአምደ ወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በሰላም ግንባታ ላይ እየተወያየ ነው።
በውይይት መድረኩ ላይ የብሔሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳሉት፤ መንግስት የሕዝብን መሰረታዊ ፍላጎት እውን እንዲሆን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ታጣቂዎች ወደ ሰላም አማራጭ መመለሰሳቸውን አንስተዋል።
የቀሩትም እንዲመለሱ መንግስት በሆደ ሰፊነት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አውስተው፤ የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉት ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል።
በአስተዳደሩ የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሰፈነውን ሰላም በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤
አሁንም ሕብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ እየሰጠ ያለው ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
የአምደ ወርቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያለው ወዳጅ እንዳሉት፤ የፅንፈኛ ቡድኑ እያከናወነ ያለው ተግባር ከሕብረተሰቡ ባሕልና ወግ ያፈነገጠ በመሆኑ ሕዝቡ አምርሮ መታገል ችሏል ብለዋል።
የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሕብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆኖ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አንስተዋል።
የሕዝቡ ዋነኛ አጀንዳው ሰላም ብቻ በመሆኑ ይህንን በመጠበቅ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ አምደወርቅና ደሃና ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተካሄደ ባለው የሰላም ግንባታ ውይይት ላይ የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮልን ጨምሮ የብሔረሰብ አስተዳደሩ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።