ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎታችችንን በማሳደግ ስራዎቻችንን በላቀ ፍጥነት እንድናከናውን አስችሎናል - ሰልጣኝ ሠራተኞች

ድሬደዋ፣ ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ):- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውንና ብቃታቸውን በማሳደግ ስራቸውን በላቀ ፍጥነት ለመወጣት እንዳስቻላቸው በድሬደዋ አስተዳደር  የተለያዩ ተቋማት ሰልጣኝ ሠራተኞች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ በመላው ሀገሪቷ የተጀመረው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ በዕውቀትና ክህሎት ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያዎች ለማፍራት መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይሄው ሀገርአቀፍ ስልጠና እንደ ሀገር የተጀመረውን ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ አበርክቶው የላቀ ነው።

የዚህ ስልጠና ተጠቃሚ የሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ስልጠናው ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በተሟላ መንገድ ዳር ለማድረስ የተጀመረውን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ አስችሏል።

ከሰልጣኞቹ መካከል የድሬደዋ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ፍቅሩ ዘውዴ  በአራት የተለያዩ  ዘርፎች የቀሰሙት የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀት በየትኛውም ዘርፍ ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የተቋማቸውን  መረጃን  በፍጥነትና በላቀ ብቃት  በቴክኖሎጂ አውታሮች ለተገልጋዮች ተደራሽ በማድረግ ማህበረሰቡ ከተቋሙ ጋር ትስስሩን እንዲያጠናክር እየሰሩ መሆኑን በመግለፅ ።

እንደ አቶ ፍቅሩ ገለፃ  ኢትዮ ኮደርስ አገራዊውን የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም በተሟላ መንገድ ለመተግበር የተጀመረውን ስራ ለማሳካትም የሚያስችል በመሆኑ ሠራተኞች ስልጠናውን በአግባቡ መከታተል ይገባቸዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የዳታ አጠናቃሪ  አቶ ከድር ሙስጠፋ  እና  ስልጠናው የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀታቸውን በማጎልበት በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ስልጠናው ከስራ ውጭ ባሉ ሰአታት ተደራሽ መደረጉ ደግሞ የመንግሥት ሰራተኛውን ሆነ በየትኛውም ዘርፍ የተሰማራውን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በማስታወስ ።

የአስተዳደሩ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አሸናፊ አበራ በበኩላቸው ቴክኖሎጂ እንዳይቀድመን እኛ ቀድመን እንድንገኝ አስችሎናል ብለዋል።

በነፃ እየተሰጠ የሚገኘው የቴክኖሎጂ ስልጠና የትኛውንም ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያስችል አቶ አሸናፊ አክለው ተናግረዋል ።

ስልጠናው ከስራ ሰአታት ውጭ  ተደራሽ መደረጉ ደግሞ ከዋናው ስራ በተጓዳኝ የመንግሥት ሰራተኛውን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በማስታወስ።

በድሬዳዋ አምና 4ሺህ 600 የሚሆኑ ወጣቶችና ሠራተኞች ስልጠናውን በስኬት አጠናቀው የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መቀበላቸው ከድሬደዋ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ዘንድሮም ከ17ሺህ 600 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ስልጠናውን  ለመከታተል መመዝገባቸውንና ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በስልጠና ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም