ቀጥታ፡

ማዕከሉ የገብስ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የመነሻ ዘር ብዜት እያከናወነ ነው

ሮቤ፤ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የገብስ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የመነሻ ዘር ብዜት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

ማዕከሉ በተለይ ከዚህ ቀደም በምርምር ከለቀቃቸው ዝርያዎች መካከል 15 የተለያዩ የቆሎና የብቅል ገብስ ዝርያዎች ይገኙበታል።

የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ሚደቅሳ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በምርምር እየደገፈ ነው።


 

በተለይ ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በስንዴ፣ በገብስና በሌሎች ስምንት የትኩረት መስኮች ላይ ምርምሮችን በማካሄድ 116 የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ በአዲስ መልኩ እያከናወናቸው ከሚገኙ የምርምር ተግባራት በተጓዳኝ ከዚህ ቀደም በምርምር ያገኛቸውን የሰብል ዝርያዎች አርሶ አደሩ ዘንድ ተደራሽ ለማድረግ 200 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የመነሻ ዘር ብዜት እያካሄደ መሆኑን በማሳያነት አቅርቧል።

በተለይም ባለፉት ዓመታት ባካሄዳቸው ውጤታማ ምርምሮችና በተፈጥሮ ባለው ምቹ ስነ-ምህዳር ብሔራዊ የገብስ ምርምር አስተባባሪ ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በዚህ ዓመትም የገብስ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎችን በስፋት እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ማዕከሉ በገብስ ዝርያ ላይ የሚደረጉትን ምርምሮች እያስተባበረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ ተመራማሪና የብሔራዊ የገብስ ምርምር አስተባባሪ ወይዘሮ ህይወት ሰብስቤ ናቸው።

የሲናና ግብርና በተለይ ባለፉት ዓመታት በገብስ ላይ ባካሄደው ውጤታማ ምርምር ዘጠኝ የምግብ ገብስ፣ ሁለት የቆሎና አራት የብቅል ዝርያ ገብስ ለተጠቃሚዎች ማድረሱን አመልክተዋል።

በማዕከሉ ከተለቀቁት የምግብ ገብስ መካከል በአንድ ሄክታር እስከ 65 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ''ወለሼ''ና ''ጌሴ'' የሚል ስያሜ የተሰጣቸው እንደሚገኙበት አስታውሰዋል።


 

እንዲሁም የብቅል ፋብሪካ ፍላጎትን የሚያሟሉና በአንድ ሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጡ ''ሲንግተን''ና ''ሞአታ'' የሚል ሲያሜ ያገኙ የብቅል ገብሶችንም ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ህይወት እንዳሉት፣ ሲናናን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የምርምር ማዕከላት ባለፉት ዓመታት በገብስ ዝርያ ላይ ባከናወኗቸው ምርምሮች ለምግብ ፍጆታነት ከማዋል ባሻገር ከውጭ ይገባ የነበረውን የብቅል ገብስ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ በማዳን ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም