ቀጥታ፡

ፋይዳ መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-ፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለፁ።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ የሴቶች ንቅናቄና የግንዛቤ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን እንዳሉት፥ የፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ፋይዳ ለሴቶች፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች የእኩልነት መብት ማረጋገጫና የማስፈፀሚያ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ህብረተሰብ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያ ሥላሴ በበኩላቸው፥ መንግስት ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ዲጂታል መታወቂያ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ማንኛውም ሰው ራሱን የሚገልጽበትና መብቱን የሚያረጋግጥበት መለያ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ወደ ዞንና ወረዳ ድረስ በመውረድ የመመዝገብ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባን ለማሳካት የሴቶች ተሳትፎ ቁልፍ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ለፋይዳ መታወቂያ ከተመዘገቡ ዜጎች መካከል 40 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም