ቀጥታ፡

የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የምናበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን-የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 7/2018(ኢዜአ)፡-የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ሥራዎች ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ያልተሳተፉ አካላት፣ የትግራይ ክልል ሕዝብና በተለያየ ምክንያቶች ከመሳተፍ የታቀቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ለማድረግ ተጨማሪ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው።

ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የያዛቸው ትልሞች ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ እንዲያጠናቅቅ የጋራ ምክር ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

የብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ እስከአሁን ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ የዲሞክራሲ ሥርዓቱን ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተው፤ ፓርቲያቸው ለስኬታማነቱ ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን ታፈሰ እንደተናገሩት፤ ፓርቲያቸው በምክክር ሂደቱ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።

በምክክር ሂደቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ወገኖች እንዲሳተፉ ፓርቲያቸው እየሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች በምክክር ሂደቱ ሳይሳተፉ የቀሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ ፓርቲው የበኩሉን ሚና ለመጫወት አበክሮ ይሰራል ነው ብለዋል።


 

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ አዲስ መሀመድ እንደገለጹት፤ ምክክሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ሲሆን፤ ፓርቲያቸው ለስኬታማነቱ ይሰራል።


 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ይህን በመገንዘብ ፓርቲያቸው በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቁመው፥ቀሪ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም