ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታችንን አሳድጎታል-ሰልጣኞች

አሶሳ፤ታህሳስ 7/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎታቸውን በማሻሻል ተወዳዳሪነታቸውን እንዳሳደገው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰልጣኞች ተናገሩ።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተነደፈው የ5 ሚሊዮን ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተቀመጡት የ100 ፐርሰንት ግቦች አንዱ ነው።

ይህም የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ እንዳደረጋቸው ስልጠናውን የወሰዱ ዜጎች ይገልጻሉ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ስልጠናውን ከወሰዱ ሰዎች መካከል የሻምበል በዛብህ እንደገለፀው፥የ5 ሚሊየን ኮደርስ ኢንሼቲቭ የዜጎችን የዲጂታል ዕውቀት በማሳደግ ወቅቱ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለመፍጠር ያግዛል።

ስልጠናው ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ዜጎች የዲጂታል ዕውቀታቸውን በማዳበር አዳዲስ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን ለማልማት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከኢትዮ-ኮደርስ ኢንሼቲቭ ኮርሶች አራቱን ያጠናቀቀው ሌላው ሰልጣኝ ብርሃኑ ሽታነህ እንዳለው፥ የኢትዮ -ኮደርስ ኢንሼቲቭ ዜጎች ራሳቸውን ለማብቃት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ብለዋል።

ስልጠናው መደበኛ ስራውን ለማሳደግና በትርፍ ጊዜው የጀመረውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ አቅም እንደፈጠረለት ተናግሯል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሶስት ዓመት ውስጥ 65 ሺህ ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ሳይንስ፤ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ይታያል በላይ ናቸው።

በክልሉ እስካሁን ድረስ ከ12 ሺህ 200 በላይ ዜጎች ስልጠናውን እየተከታተሉ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል የዜጎችን አቅም ከማሳደግ ባለፈ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ለተያዘው ዕቅድ ወሳኝ በመሆኑ የዜጎችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በክልሉ የኮደርስ ስልጠናን በተቀናጀ ሁኔታ ለማስኬድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም