የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 54 የአገልግሎቱ ሠራተኞች ላይ ርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 54 የአገልግሎቱ ሠራተኞች ላይ ርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ያለፉት አምስት ወራት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዲጂታል የሙስና መረጃ (ጥቆማ) መቀበያ ሥርዓት እና በሌሎች አማራጮች ከቀረቡ ጥቆማዎች ውስጥ 54 አመራርና ሠራተኞች ጥፋተኛ መሆናቸውን ተረጋግጦ ርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር፤ የተወሰደው ርምጃ 10 የጽሑፍ፣ 37 የደመወዝ፣ 2 ከቦታ የማንሳት፣ 5 ስንብት መሆኑን አብራርተዋል።
ከሥራ እንዲሰናበቱ የተደረጉት ሠራተኞች በሥነ-ምግባር ጥሰት ምክንያት መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
ይህም የጥቆማ መቀበያ ሥርዓቱ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ፣ ደንበኞች የሚሰጡት ጥቆማ ዋጋ ያለው መሆኑን እና የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ለመታገል ተቋሙ እያደረገ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አሥተዳደር ችግርና ብልሹ አሠራሮችን ለመታገልና ርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ተገልጋዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሰል ችግሮችን ሲመለከቱ በተዘረጋው ዘመናዊ የሞባይል መተግበሪያ ወይም www.eeuethics.et ላይ በመጠቆም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።