በካራባኦ ዋንጫ ካርዲፍ ሲቲ ከቼልሲ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በካራባኦ ዋንጫ ካርዲፍ ሲቲ ከቼልሲ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ካርዲፍ ሲቲ ከቼልሲ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በካርዲፍ ስታዲየም ይካሄዳል።
ካርዲፍ ሲቲ በአራተኛው ዙር ሬክሳምን 2 ለ 1 አሸንፏል። ቼልሲ ዎልቭስን 4 ለ 3 ረቷል።
የዌልሱ ክለብ ካርዲፍ ሲቲ የካራባኦ ዋንጫን አንስቶ አያውቅም። እ.አ.አ በ2011/12 ለፍጻሜ ደርሶ በሊቨርፑል የተሸነፈ ሲሆን ብቸኛው ለዋንጫው የተጠጋበት አጋጣሚም ነበር።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ አምስት ጊዜ የካራባኦ ዋንጫን አንስቷል። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የነበረው እ.አ.አ በ2014/15 ነበር።
የካራባኦ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ነገም ሲቀጥል ማንችስተር ሲቲ ከብሬንትፎርድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ከፉልሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዚህ ሳምንት ሊደረግ የነበረው የአርሰናል እና ክሪስታል ፓላስ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ ተደራራቢ ጨዋታዎች ስለበዙብኝ ይራዘምልኝ ብሎ ለአወዳዳሪው አካል ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ወደ ቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግሯል።
እ.አ.አ በ1960 የተጀመረው የካራባኦ ካፕ (በቀድሞ አጠራሩ የእንግሊዝ ፉትቦል ሊግ ዋንጫ) በእንግሊዝ ከአንጋፋው ኤፍ ካፕ ውጪ የሚደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው።
ሊቨርፑል 10 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው። ማንችስተር ሲቲ ስምንት እና ማንችስተር ዩናይትድ ስድስት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ይከተላሉ።