ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

አርባምንጭ፤ ታህሳስ 7/2018 (ኢዜአ) ፡-የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገለጸ።

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራ በተጓዳኝ በማህበረሰብ አገልግሎት ስራው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ መስራት ይገባቸዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ሲሆን በዚህም በጋሞ፣ በጎፋ፣ በባስኬቶ፣ በኮንሶ፣ በጋርዱላና በአሌ ዞኖች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በጋሞ ዞን ካምባ ዙሪያ ወረዳ ድንጋሞ ቀበሌ ከ400 በላይ ነዋሪዎችን የሃይል ተጠቃሚ ያደረገ 15 ኪሎ ዋት የሚያመነጭ ታዳሽ ሃይል ፕሮጀክት ገንብቶ በቅርቡ ለአገልግሎት ማብቃቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በገጠር የሚገኙ ማህበራዊ ተቋማትን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነ ተግባርም በአጎራባች ዞኖች የሚገኙ 24 ጤና ጣቢያዎችና 19 ትምህርት ቤቶችን የሶላር ሃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የእንሰት መፋቂያና ማብላያ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በማላመድም በአምራች አርሶ አደሮች ላይ ይደርስ የነበረውን የጊዜና ጉልበት ብክነት በመቀነስ የቆጮ ማብላያ ሂደትን ማሳጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂው በመታገዝ ከእንሰት ምርት ኩኪስና ሌሎች ምግቦችን መስራት መቻሉን ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂው ለብዙዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑም እንሰት አምራች በሆኑ በሲዳማና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ሙዝን ወደ ዱቄት የሚቀይር ቴክኖሎጂ በመፍጠርም ዜጎች የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡

በጋሞና ወላይታ ዞኖች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በ100 ሄክታር መሬት ላይ ሃሌኮ ወይም ሽፈራው ቅጠልን ሜካናይዝድ በሆነ መንገድ የማልማት ስራን ጨምሮ በምርምር የታገዘው የተጎዳ አፈርን ለማከም የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ውጤታማ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዞኑ ሥር የሚገኙ የገዜ ጎፋ፣ የመሎ ጋዳ እና መሎ ኮዛ ወረዳ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል። 

በተለይም የጤና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው የመሎ ጋዳ ወረዳ ጤና ጣቢያን የሶላር ተጠቃሚ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አጠገባችን የሚገኘውን የድንጋሞ ወንዝ ተጠቅሞ የሃይል ተጠቃሚ አድርጎናል ያሉት ደግሞ በጋሞ ዞን ካምባ ዙሪያ ወረዳ የድንጋሞ ቀበሌ አስተዳደር አቶ ከድር ካማ ናቸው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም