ቀጥታ፡

የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 7/2018 (ኢዜአ)፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በዋናነት የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ከጥቃት መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር መከላከል ዳይሬክተር መሀመድ ፈረጃ፤ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል በተለይ ቁልፍ መሠረተ-ልማት ላይ የሚከናወኑ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሀገራችን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን ዐዋቅራ እየሠራች ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በዲጂታል 2025 ላይ የጸደቀው ስትራቴጂ የሳይበር ደኅንነትን እንደ አንድ ምሰሶ ወስዶ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሠራበት እና ተቋማት የየራሳቸውን ኢኒሼቲቭ ቀርጸው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ጭምር እያስቻለ መሆኑን አመላክተዋል።

በ2024 የጸደቀው የግል መረጃዎች ጥበቃ ዐዋጅ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶች ባለቤቶች ለሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጡ በመጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተዘጋጀ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶች ጥበቃ ረቂቅ ዐዋጅ መኖሩንም ጠቁመው፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በዚህ ዓመት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ብለዋል።

ይህም ቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ለመጠበቅ ከፍተኛ ዐቅም እንደሚሆን ነው ለኢዜአ የተናገሩት።

በተጨማሪም በሴክተሮች ላይ ምን ዓይነት አዳዲስ ስጋት አለ? የሚለውን በመከታተል በሴክተሮቹ ላይ የሚያጋጥመውን ስጋት ከሴክተሩ ባለቤት ጋር በመሆን የመቀነስ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ያለውን የክኅሎት ክፍተት ለመሙላት ተቋሙ ከትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ የሳይበር ደኅንነት ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም