ቀጥታ፡

ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈጸም በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ዝግጅት ተጀምሯል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲፈጸም በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ዝግጅት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

‎‎‎በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የተጻፈ "የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና" የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።


 

‎በመጽሐፍ ምረቃ ወቅት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ‎ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ በመንግሥት በፀጥታ ተቋማት ላይ ውጤታማ ሪፎርም መካሄዱን ገልጸዋል።

‎ይህ ሪፎርም የፀጥታ ተቋማት በነጻነት፣ በሰብዓዊ መንገድ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ማስቻሉን ተናግረዋል።


 

ባለፈው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲፈጸም የፀጥታ ተቋማት የላቀ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።

‎በቀጣይ የሚካሄደው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲከናወን ዝግጅት መጀመሩንም ገልጸዋል።

‎"የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና" የተሰኘው መጽሐፍ ፖሊሳዊ ሪፎርም በተካሄደበት ወቅት መመረቁ ሪፎርሙን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

‎መጽሐፉ በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ለፀጥታ አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም