የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ጉዳይ ነው- ሚኒስትር አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ጉዳይ ነው- ሚኒስትር አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ)፦የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲመዘገቡ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።
በሚቀጥሉት 3 ወራት 12 ሚሊየን አርሶና አርብቶ አደሮች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ ግብ መያዙንም ጠቅሰዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራምና ከክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ዲጂታል መታወቂያን በገጠር ለማስፋት እና ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በተያዙ ግቦች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ እንዳሉት የግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ስኬታማ ለማድረግ ዲጂታል መታወቂያን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
አርሶ እና አርብቶ አደሩ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ የሚያደርገውን የዲጂታል መታወቂያ በመመዝገብ እንዲይዝ ለማድረግ የተቀናጀ ስራ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
ፋይዳ መታወቂያ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን፣ የገጠር ፋይናንስን የአርሶ አደሮች መረጃ አያያዝን፣ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ከ12 ሚሊየን በላይ የገጠር ነዋሪዎች የብሔራዊ መታወቂያ እንዲመዘገቡ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ተረጅነትን ዜሮ በማድረስ ግብ መሰረት ከአራት ሚሊዮን በላይ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን እስከ ታህሳስ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከተረጅነት ለማላቀቅ ግብ መቀመጡን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ክልሎች የተቀናጀ ስራን ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት እስከ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም ድረስ የፋይዳ መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን 90 ሚሊየን ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸው በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ለታቀደው ግብ መሳካት የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የፋይናንስ ተደራሽነት፣ የግብርና ግብዓት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን፣ ለማፋጠን ዲጂታል መታወቂያ ትልቅ አስተዋዕጾ እንዳለው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው በክልሉ የገጠር ነዋሪዎችን የዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ከታቀደው በላይ ለመፈጸም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በክልሉ በሴፍቲኔት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ነው ያነሱት።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው አርሶና አርብቶ አደሩን ከተረጂነት ለማላቀቅ እና አምራችነትን ለማበረታታት የተጀመሩ ስራዎች በክልሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።
ዘመናዊ አርሶ አደር ለመፍጠር ወሳኝ የሆነውን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ለማሳካት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው ከተረጂነት ለመላቀቅ የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ ናቸው።
ዲጂታል መታወቂያን በተመለከተ ግንዛቤን በማጠናከር አርሶና አርብቶ አደሩ በስፋት እንዲመዘገብ እንተጋለን ብለዋል።