በክልሉ ብቁና ውጤታማ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ብቁና ውጤታማ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባሕር ዳር ፤ ታሕሳስ 6/2018 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ከሲዳማ ክልል የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አመራርና አባላት የባሕር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲዮም የማጠናቀቂያ ስራዎችን በመጎብኘት የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ አድርገዋል።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ በወቅቱ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ ለስፖርት ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ታዳጊዎች ላይ መሰረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ከ90 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትና ፕሮጀክቶች መቋቋማቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ላይ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለፕሮጀክቶች ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ክልሉን ብሎም ሃገርን የሚወክሉ ብቁና ውጤታማ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል በተከናወኑ ተግባራት በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ በደባርቅ፣ በደብረብርሃን፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አካባቢዎች በተቋቋሙ ፕሮጀክቶች ከታቀፉ ታዳጊዎች አትሌቶችና የእግር ኳስ ተጨዋቾችን ማፍራት እንደተቻለም ለአብነት አንስተዋል።
ከሲዳማ ክልል የመጡት አመራርና አባላትም በባሕር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲዮም የካፍና የፊፋን ደረጃ ባሟላ መልኩ እየተከናወኑ የሚገኙ የማጠናቀቂያ ስራዎችን ተመልክተው ልምድና ተሞክሮ ለመውሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የጎብኚዎቹ ቡድኑ መሪ አቶ ካሱ አሩሳ በበኩላቸው፤ አመራርና አባላቱ ከክልሉ የተለያዩ ተቋማት ተወክለው እንደመጡ ጠቅሰው፤ በዚህም የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮምን የስራ ሁኔታ በመመልከት ልምድና ተሞክሮ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ስታዲዮም ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የካፍና የፊፋን ደረጃዎች ባሟላ መልኩ የተገነባ መሆኑን እንደተረዱ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ስታዲዮም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ባሟላ መልኩ መገንባት የሚያስችል ልምድ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ናቸው።
ከስታዲዮሙ አጥር ጀምሮ የሳር ተከላ፣ የ"ቪ አይ ፒ " መግቢያዎች፣ መቀመጫዎች፣ የተጫዋቾች ማረፊያ፣ የመልበሻና ሌሎችም መገልገያዎች የካፍና የፊፋን ደረጃ ባሟላ መልኩ መገንባቱን እንደተረዱ ገልጸዋል።
አጠቃላይ የተመለከቷቸውን የማጠናቀቂያ ስራዎች ልምድና ተሞክሮ ወስደው የሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ላይ እንደሚተገብሩትም አንስተዋል።