ቀጥታ፡

መንግሥት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ግንባታውን ማፋጠኑ ተስፋችን ለምልሟል-አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግሥት ለዓመታት ተጓቶ የቆየውን የመገጭ የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ግድብ  ፕሮጀክትን በማፋጠን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እያከናወነው ያለው ሥራ ተስፋችንን አለምልሞታል ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።

ፕሮጀክቱ  የጎንደር ከተማና የአካባቢውን ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከ15 ዓመታት በፊት ነው ግንባታው የተጀመረው። 

የአካባቢው ነዋሪዎችም ከዓመታት በፊት ለንፁህ መጠጥ ውሃና ለመስኖ ልማት የሚሆን ፕሮጀክት ሊጀመር መሆኑ ሲነገራቸው ደስታቸው ወደር አልነበረውም።

ኢዜአ  ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት፥ ቀደም ብሎ ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከአራት ዓመት በኋላ እንደሚጠናቀቅና የአካባቢውን ነዋሪ የውሃ ችግር እንደሚፈታ ተነግሮን ነበር ይላሉ።

አርሶ አደር ገብሩ ዘውዱ፣ አንገብጋቢ ከሆነባቸው የውሃ እጥረት ተላቀው በክረምትና በጋ በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ በጉጉት ለዓመታት መጠበቃቸውንም አውስተዋል።

ይሁንና በአራት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለው የመገጭ መስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች በተቀመጠለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ለበርካታ ዓመታት ቆይቷል።

አርሶ አደር ተስፋዬ አዲሱና ጌታነህ ወርቄ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ በምን ምክንያት እንደዘገየ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያነሱም ተገቢ ምላሽ ሳያገኙ ዓመታት መቆጠራቸውንና በዚህም ተስፋ መቁረጣቸውን ያስታውሳሉ።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2016 ዓ.ም የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንዲከናወኑ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት እንደ አዲስ ወደ ስራ ተገብቷል።

አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት፤ መንግሥት በአዲስ መልኩ የመገጭ ግድብ ግንባታን እያፋጠነ በመሆኑ እና ቀን ከሌሊት የሚደረግ ግንባታ አፈጻጸም ከቁጭት ወጥተው ዳግም ተስፋቸው ለምልሟል።

የለውጡ መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች መሰረት ፕሮጀክቱን የተረከበው ቤ አ ኤ ካ የተሰኘው ሀገር በቀል ተቋራጭና የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን  የግድቡን ግንባታ በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራን ነው ብለዋል።


 

የፕሮጀክቱ አማካሪ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተጠሪ መሃንዲስ ወርቅነህ አሰፋ ግድቡ 185 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለውና ለመጠጥ ውሃና ለመስኖ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

አዱሱ የግንባታ ተቋራጭ የፕሮጀክቱን ችግሮች በማስተካከል ወደ ግንባታ መግባቱን ጠቅሰው፤ በፕሮጀክቱ የግንባታ ቦታ ያጋጥም ለነበረው የመሬት መንሸራተት በጥናት የተደገፈ መፍትሔ መሰጠቱን ገልፀዋል።

የግድቡን ግንባታ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የቤ አ ኤ ካ ኮንስትራክሽን የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጌታቸው አረጋና የፕሮጀክት አስተዳደር ኢንጂነር ፍቃዱ አለነ በበኩላቸው፣ ተቋራጩ የግድቡን ግንባታ በቀንና በምሽት ፈረቃ እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም  77 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ ካሳ እንደሚሉት፣ ከለውጡ በፊት እንደ ሀገር ለመስኖ ግድብ ግንባታ ወጥ የሆነ መስፈርት አልነበረም።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር  ለመስኖ ግድብ ግንባታ መስፈርት በማውጣት ፕሮጀክቶች በተያዘው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቅሰው፥ የመገጭ ግድብም ትንሳኤው ደርሷል ብለዋል።


 

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንደሚሉት፤ የመገጭ ግድብ ግንባታ ውስብስብ ቸግሮችን አልፎ አሁን ላይ ሊጠናቀቅ በጉጉት የሚጠበቅ ፕሮጀክት ሆኗል።

ፕሮጀክቱ ለጎንደርና አካባቢዋ ህዝብ ለመጠጥ ውሃና ለመስኖ ልማት የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረት መስጠታቸውን ነው ያነሱት።

ግድቡ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንዳለው ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም