የመደመር መንግሥት ጥበብ ለሀገር ብልጽግና እና እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ጥበብ ለሀገር ብልጽግና እና እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ):-የመደመር መንግሥት ጥበብ ለሀገር ብልጽግና እና እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው በግልጽ ማስቀመጡን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተዘጋጁ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ፣ሌሎች የህግ ማዕቀፎች እና በጸደቁ የአሰራር መመሪያዎች ላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂድ የቆየው ውይይት ተጠናቋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት፤ ጥበብን ለአሰባሳቢ ትርክት እና ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ቱባ ባህሎች ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ባህልን የሚበርዙ ነገሮችን በጋራ መከላከል ይገባልም ነው ያሉት።
መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለባህላዊ እሴቶች እና የጥበብ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ዘርፉን በመሰረተ ልማት፣በአደረጃጀት እንዲሁም በስርዓተ ትምህርት በማካተት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ኪነ-ጥበብ ለሀገር ብልጽግና እና እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው በግልጽ ማስቀመጡን ተናግረዋል።
በዘርፉ እየተዘጋጁ ያሉ ማእቀፎች የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ መሆናቸውንም አንስተው፤ በቀጣይ ጊዜያትም ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሀዲ፣የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሀት፣አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።