ቀጥታ፡

አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት አስችሏል    

አዶላ ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ):-አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኙ ማስቻሉን በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ ጊዜና ወጪን ከመቆጠብ ባለፈ ትኩረታቸውን በልማት ሥራዎች ላይ እንዲያደርጉ እድል የፈጠረላቸው መሆኑንም ተገልጋዮቹ ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ሰላምን ለማስፈን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ተግባራዊ ሆኖ ውጤት እየተገኘበት ነው።

አደረጃጀቱ ህዝቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።

በተለይ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹም በህዝብ ተሳትፎ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተገለጸው።

አዲሱን የቀበሌ አደረጃጀት በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በጉጂ ዞን የኦዳ ዶላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሰ ባነታ እንደገለጹት፣ በአካባቢያቸው መንግስታዊ አገልግሎት ተደራሽ መደረጉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ረጅም ርቀት ሲጓዙ የነበረውን ሁኔታ አስቀርቶላቸዋል፡፡


 

እንደ ኦሮሚያ ክልል የተጀመረው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት በዞናቸው መተግበሩ በአካባቢያቸው ሰላምና ልማት ላይ  ከመንግስት ጋር በመናበብ  እንዲሰሩ ዕድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

አደረጃጀቱ መንግስታዊ አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን ማገዙንና ነዋሪውም ጊዜውን በልማት ላይ እንዲያሳልፍ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታከለ ኤልያስ ናቸው።


 

የቀበሌ አደረጃጀቱ ልማትን ለማስቀጠልና ባህላዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ  የራሱን  ፋይዳ  ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡

በተለይም አለመግባባቶች በቅርበት በአባገዳዎችና በሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈቱ የባህላዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስርአት  መተግበሩን አስረድተዋል፡፡

የቀበሌ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማት፣ የፍትህ አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት እንዲመለሱ እድል በመስጠቱ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ነው የተናገሩት።

የኦዳ አዶላ ቀበሌ ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ዱረቲ አሬሪ ፤በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶች በመካተታቸው ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ አገልግሎትን በቅርበት ለመስጠት ማስቻሉን  ጠቁመዋል፡፡


 

በተለይ የፍትህ፣ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለህዝብ በቅርበት ለመመለስ አደረጃጀቱ ፋይዳው የጎላ  ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም ባለፉት አምስት ወራት ለማህበራዊ ፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 170 የክስ መዝገቦች 150 ዎቹ አፋጣኝ የፍትህ ውሳኔ ማግኘታቸውን  ጠቁመዋል፡፡

በህዝብ ተሳትፎ የገጠር መንገድ፣ የመጠጥ ውሀ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የመሸጫና የማምረቻ ቦታ መመቻቸቱን እንዲሁም  ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ   መቅረቡንም ጠቅሰዋል፡፡


 

የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ብዙነህ  በበኩላቸው፤ በዞኑ በህዝብ ተሳትፎ 267 የቀበሌ ጽህፈት ቤቶች መገንባታቸውን  ገልጸዋል፡፡ 

ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት 267 ባህላዊ ፍርድ ቤቶችና 13 ይግባኝ ሰሚ ችሎት መቋቋሙን ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህም የዞኑን ህዝብ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች  በቅርበት እንዲመለሱ ማገዛቸውን ነው የገለጹት።

አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የዞኑን ህዝብ አኗኗር፣ የሥራ ባህል፣ የፍትህ አገልግሎት እንዲሁም የሰላምና የልማት ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም