የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ዕይታ አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና የጎብኝዎች መዳረሻ አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ዕይታ አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና የጎብኝዎች መዳረሻ አድርጓታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2018(ኢዜአ):- የመደመር መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በመዲናዋ አስደናቂ የመስህብ ስፍራዎችን በመገንባት የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና የጎብኝዎች መዳረሻ እንድትሆን ማስቻሉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የመደመር መንግሥት በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዕይታው ትኩረት ከሰጣቸው የልማት መስኮች አንዱ ቱሪዝም ነው።
በቱሪዝም ዘርፍ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ኢኒሼቲቭ ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል።
በአዲስ አበባም በመደመር እሳቤ ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን ደረጃቸውን ጠብቆ በማደስ ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ አስደናቂ የሆኑ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት በመዲናዋ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
በተለይም ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችና የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነትና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በሚመጥን መልኩ ፈጣን ለውጥ እንድታመጣ ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተገነቡት አንድነት ፓርክና ሌሎችም ፓርኮች እንዲሁም የብሔራዊ ቤተመንግሥት ታድሶ መከፈት ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።
የጥበብ ማሳያ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ አምፊ ቴአትሮችና ሌሎች የቱሪዝም የልማት ስራዎች የመደመር መንግስት ውጤት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የጎብኝዎችን ቆይታ ከማራዘም ባለፈ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አቅም ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባን የዓለም አቀፍና የአህጉራዊ ጉባኤዎች ማዕከል የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ የድል ታሪካችንን እና የአፍሪካውያንን የነጻነት ታሪክ ከመዘከር ባለፈ ታላላቅ ጉባኤዎች የሚካሄዱበት ሥፍራ ሆኗል ብለዋል።
አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልም ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችንና ሌሎችንም ኹነቶች በማስተናገድ አዲስ አበባን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።