ቀጥታ፡

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዲስ አበባ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ማህሌት ምትኩ በ35ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥራለች።

በጨዋታው ላይ ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ማህሌት ምትኩ የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።

በውድድር ዓመቱ 11ኛ ድሉን ያስመዘገበው የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን ወደ 33 ከፍ አድርጓል።

በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ዛሬ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።

የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም